League Table

ደ ዜርቢ ቶተንሃሞች ከሊጉ ላለመውረድ በሚያደርጉት ወሳኝ ጨዋታ “ለክብራችሁ ተጫወቱ” ሲል አሳሰበ

ሮቤርቶ ደ ዜርቢ ቶተንሃም ከኤቨርተን ጋር የሚያደርገው የመጨረሻ ቀን የሊጉ ጨዋታ ባለፈው የውድድር ዘመን ማንቸስተር ዩናይትድን ከገጠሙበት የዩሮፓ ሊግ ፍጻሜ የበለጠ ትልቅ ዋጋ እንዳለው ገለጹ። እንደ አሰልጣኙ ገለጻ የክለቡ አጠቃላይ ክብር አሁን በሚደረገው ጨዋታ ላይ የተመሰረተ ነው። ማክሰኞ ምሽት በቼልሲ 2 ለ 1 የተሸነፉት ስፐርሶች፣ በሊጉ ለመቆየትና ዌስትሃም ወደ ታችኛው ሊግ እንዲወርድ ለማድረግ እሁድ በሚያደርጉት ጨዋታ አቻ መውጣት ብቻ ይበቃቸዋል። ከነሱ በሁለት ነጥብ ዝቅ ብለው በመውረጃ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ሃመርስ (ዌስትሃም)፣ የግብ ክፍያቸው በእጅጉ ያነሰ ሲሆን የመጨረሻ ጨዋታቸውን በሜዳቸው ከሊድስ ጋር ያደርጋሉ።

ስፐርሶች ከ17 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያውን ዋንጫ በቢልባኦ ዩናይትድን አሸንፈው ሲያነሱ ደማቅ አከባበር የነበረ ቢሆንም፣ ደ ዜርቢ ግን በፕሪሚየር ሊጉ መቆየት መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን በግልጽ ተናግረዋል። “ትኩረቴ የሚቀጥለውን ጨዋታ በማዘጋጀት ነጥብ ማግኘት ላይ ነው፤ ምክንያቱም እሁድ ለቶተንሃም የፍጻሜ ጨዋታ ነው እንጂ በቢልባኦ ከማን ዩናይትድ ጋር የነበረው ጨዋታ አይደለም” ብለዋል ደ ዜርቢ። “ከሁሉ በላይ አስፈላጊው ጨዋታ የእሁዱ ነው፤ ባለፈው የውድድር ዘመን ለዋንጫ ተጫውተዋል፣ አሁን ግን ከዚያ የበለጠ ዋጋ ላለው ነገር እንጫወታለን። ምክንያቱም የክለቡ ኩራት፣ ታሪክና ክብር ከዋንጫ የበለጠ ዋጋ አላቸው።”

“ዋንጫ ልታሸንፍ ወይም ልትሸነፍ ትችላለህ፣ ይህም በህይወትህ ላይ ምንም የሚቀይረው ነገር የለም፤ አንድ ተጨማሪ ዋንጫ ሊኖርህ ይችላል። ነገር ግን ከሁሉ በላይ አስፈላጊው ክብርንና ኩራትን ጠብቆ መቆየት ነው፤ ከጨዋታ በኋላ ወደ እረፍት ስትሄድም አንገትህን ቀና አድርገህ እንጂ አቀርቅረህ መሆን የለበትም” ሲሉ አክለዋል። ደ ዜርቢ ተጫዋቾቹ ‘ክብር’ ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ ተረድተው እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “በጣም በሚገባ ተረድተዋል” ብለዋል። “እንደሚረዱኝ አውቃለሁ ምክንያቱም የምኖረው ለቶተንሃም ብቻ ነው። ያለፉትን 45 ቀናት የኖርኩት ለአንድ ነገር ብቻ ነው – ለቶተንሃም እና ለተጫዋቾቼ። ሁሉንም በደንብ አውቃቸዋለሁ። እያንዳንዳቸውም ግባቸው ላይ ትኩረት አድርገዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ደ ዜርቢ ጨዋታው 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ሊጠናቀቅ አካባቢ ሚኪ ቫን ደ ቬን በቼልሲው ተከላካይ ማርክ ኩኩሬላ የማዕዘን ምት ላይ ተገፍቶ ቢወድቅም ቅጣት ምት (ፔናሊቲ) አለመሰጠቱን አስመልክቶ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም። ዳኛው ስቱዋርት አትዌል ጥፋቱ የተፈጸመው ኳሱ ወደ ጨዋታ ከመግባቱ በፊት ነው በሚል ብይን ሰጥተው ነበር። ይልቁንም ደ ዜርቢ ትኩረት ያደረጉት ተጫዋቾቻቸው በመጨረሻው ሰዓት ባሳዩት ብርቱ ጥረት ላይ ሲሆን፣ በዚህም ሪቻርሊሰን በ74ኛው ደቂቃ ግብ በማስቆጠር የጎል ልዩነቱን ማጥበብ ችሎ ነበር።

“እሁድ የምናደርገው ጨዋታ ልክ እንደ መጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች ቢሆን ደስ ይለኛል፤ ምክንያቱም በነዚያ 20 ደቂቃዎች ውስጥ የበለጠ ጉልበት፣ ስሜትና በውስጣችን ያለውን ተጨማሪ አቅም ያሳየን ይመስለኛል” ብለዋል ደ ዜርቢ። “ከባድ ቢሆንም ለእያንዳንዳችን ትልቅ ዕድል ነው። ከሊጉ ላለመውረድ ስትዋጋ እስከ ውድድር ዘመኑ የመጨረሻ ጨዋታ የመጨረሻ ደቂቃ ድረስ በሊጉ ውስጥ ለመቆየት መታገል አለብህ። በህይወት መቆየት አለብን። ይህ ለእኛ ትልቅ ቀን ነው” ሲሉ ንግግራቸውን አጠቃለዋል።