League Table

“ይህ ገና ጅማሮ ነው” – ሚኬል አርቴታ ከአርሰናል ጋር አዲስ ውል ተፈራረመ

ሚኬል አርቴታ ከአርሰናል ጋር እስከ 2030 ዓ.ም በክለቡ እንዲቆይ የሚያደርገውን አዲስ የረጅም ጊዜ ውል ከፈረመ በኋላ “ይህ ገና ጅማሮ ነው” ሲል ቃል ገብቷል። ስፔናዊው አሰልጣኝ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት በክለቡ የሚያቆየውን ስምምነት መፈረሙ ታውቋል። ይህም አርሰናል ለ22 ዓመታት የቆየውን የሊጉን ዋንጫ የመናፈቅ ጉጉት አብቅቶ ባለፈው የውድድር ዘመን ሻምፒዮን መሆኑን ተከትሎ የተደረገለት ከፍተኛ የደመወዝ ጭማሪን ያካተተ ነው።

እ.ኤ.አ. በታህሳስ 2019 ኡናይ ኤምሬን ተክተው ወደ መድፈኞቹ ቤት የመጡት አርቴታ፣ ፔፕ ጋርዲዮላ ከማንቸስተር ሲቲ መልቀቁን ተከትሎ አሁን ላይ በፕሪሚየር ሊጉ ረጅም ጊዜ ያገለገሉ አሰልጣኝ ሆነዋል። ምንም እንኳን ባለፈው የውድድር ዘመን በሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ በፓሪስ ሴንት ዠርሜን በፔናልቲ ቢሸነፉም፣ የ44 ዓመቱ አሰልጣኝ በአርሰናል አሸናፊ ስርወ-መንግስት ለመገንባትና ተጨማሪ ስኬቶችን ለማስመዝገብ አልመዋል። አርቴታ ቀደም ሲል በአርሰን ቬንገር ስር የክለቡ አምበል ሆኖ ማገልገሉ ይታወሳል።

አርቴታ ስለ ስምምነቱ ሲናገር “የወደፊት ህይወቴን ለዚህ ክለብ አሳልፌ መስጠቴና ለአርሰናል መልካሙን ለሚመኙ ልዩ ሰዎች ጋር መስራቴ ትልቅ ክብር ነው” ብሏል። “ይህ ክለብ ልዩ ነው፤ ባህሪውና የሚፈጥርብህ ስሜት የተለየ በመሆኑ አብረን የምንቀጥል በመሆኑ ትልቅ ኩራት ይሰማኛል። ቀድሞውንም ልዩ ትስስር ፈጥረናል፤ ለዘላለም የሚቆዩ ትውስታዎችንም አሳልፈናል፤ አሁን ላይ ይበልጥ የሚያስደስተው ግን ይህ አብረን ልናሳካው የምንችለው ነገር ጅማሮ ብቻ መሆኑ ነው” ሲል አክሏል። “ይህ ለእኔና ለቤተሰቤ የኩራት ወቅት ነው። ከአስደናቂ ደጋፊዎቻችን ፍቅርና አክብሮት ይሰማኛል፤ እኔም ሆንኩ እኛም ለደጋፊዎቻችን ያንኑ አይነት አክብሮትና ፍቅር እንመልሳለን።”

በዚህ የውድድር ዘመን መጨረሻ ሊጠናቀቅ የነበረው የአርቴታ የቀድሞ ውል በዓመት 10 ሚሊዮን ፓውንድ ደመወዝ እና ለሻምፒዮንስ ሊግ በማለፉ 5 ሚሊዮን ፓውንድ ቦነስ የሚያስገኝ ነበር። አዲሱ ውል ግን በዓለም ላይ ከፍተኛ ተከፋይ ከሆኑ አሰልጣኞች ተርታ እንዲሰለፍ ያደርገዋል። የአርሰናል የቦርድ ሰብሳቢዎች የሆኑት ስታን እና ጆሽ ክሮንኬ በበኩላቸው “እስካሁን ያደረግነው ጉዞ አስገራሚ ነበር፤ በዚህ ልዩ ግንኙነት ወደፊት የሚጠብቀን ነገርም ያስደስተናል” ብለዋል።

አክለውም “ባለፈው የውድድር ዘመን በአርሰናል ታሪክ ውስጥ ድንቅ ወቅት ነበር፤ ለዘላለም የሚኖሩ ትውስታዎችንም ፈጥረናል። ወደፊትም ተጨማሪ ስኬቶችን ለማስመዝገብ ቆርጠን ተነስተናል። ከሚኬል ጋር ልዩ ትስስር አለን። እ.ኤ.አ. በ2019 ወደ ክለቡ ከተመለሰ ጀምሮ ባስመዘገብናቸው ውጤቶች ሁሉ እንኮራለን። የአርሰናልን እሴቶች ጠንቅቆ ያውቃል፤ በልቡም ይሸከማቸዋል። ይህ ክለብ ከእሱ ጋር ግንኙነት ላላቸው ሁሉ ምን ማለት እንደሆነ ይረዳል፤ አብረን ያሳካናቸውን ነገሮች ይበልጥ ለማሳደግም ቁርጠኛ ነው” ሲሉ ገልፀዋል።

አርሰናል በዚህ ሳምንት የኤምሬትስ ስታዲየምን ለማስፋፋት የነበረውን ዕቅድ ለጊዜው ማገዱን አረጋግጧል። ይህም አርቴታ ስታዲየሙ በሚታደስበት ወቅት ወደ ሌላ ሜዳ ለጊዜው መዘዋወር በቡድኑ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን መስተጓጎል በመስጋቱ እንደሆነ ይታመናል። መድፈኞቹ ከዓለም አቀፍ የእረፍት ቀናት በፊት በብራይተን 3 ለ 0 ተሸንፈው የነበረ ሲሆን፣ ቅዳሜ ዕለት ከሊድስ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጥራሉ።