ቼልሲ በሮማን አብራሞቪች ዘመን ለፈጸማቸው በርካታ የደንብ ጥሰቶች በሐምሌ ወር በእግር ኳስ ማህበሩ (FA) የ10 ሚሊዮን ፓውንድ ቅጣት ተጥሎበታል። በተጨማሪም በሁለት የዝውውር መስኮቶች ተጫዋች እንዳያስፈርም የታገደ ሲሆን፣ በመጋቢት ወር ደግሞ በፕሪሚየር ሊጉ የ10.75 ሚሊዮን ፓውንድ ቅጣት ተላልፎበታል።
ክለቡ ከ2009 እስከ 2022 ባለው ጊዜ ውስጥ ፈቃድ የሌላቸውን ወኪሎች እንደተጠቀመና የዝውውር ስራዎቹን ምንነት ለመደበቅ እንደሞከረ ተደርሶበታል። እንደ ኤደን ሃዛርድ፣ ዊሊያን፣ ዴቪድ ልዊዝ እና ኔማንያ ማቲች ያሉ ተጫዋቾች ወደ ስታምፎርድ ብሪጅ ያመሩባቸው ዝውውሮች ከደንብ ውጭ ከተከናወኑት መካከል ይጠቀሳሉ። እነዚህ ተጫዋቾች በአንቶኒዮ ኮንቴ ስር ለተገኘው የ2016-17 የሊግ ድል ወሳኝ ተጫዋቾች ነበሩ።
የክለቡ አዲሱ ባለቤት ብሉኮ (BlueCo) ክለቡን ከአብራሞቪች ሲረከብ ቅጣቱን ለማቅለል በማሰብ ጥሰቶቹን ለሚመለከተው አካል ራሱ ያሳወቀ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ክለቡ የነጥብ ቅጣት ሳይጣልበት ቀርቷል። በአሁኑ ወቅት የዩኤስ ብሄራዊ ቡድንን እያሰለጠኑ የሚገኙት ፖቼቲኖ ግን የተወሰደው እርምጃ በቂ አይደለም ብለው ያምናሉ። የእሳቸው ቶተንሃም በወቅቱ በሰባት ነጥብ ዝቅ ብሎ ነበር ያጠናቀቀው።
ፖቼቲኖ በሰጡት ሰፊ ቃለ ምልልስ “አንድ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ማሸነፍ ነበረብን፣ ሊሰጠን ይገባ ነበር” ብለዋል። “የቼልሲ የደንብ ጥሰት እውነት ከሆነ በዚያ ዓመት ሻምፒዮን መሆን የሚገባን እኛ ነን። ተቀጥተዋል፣ ጥፋታቸውንም አምነዋል? እንግዲህ ጉዳዩ በዚህ ሊያበቃ ይገባል። ዋንጫው ሁለተኛ ለወጣው ቡድን ሊሰጥ ይገባል” ሲሉ አክለዋል።
“ጎል አግብተዋል፣ ጨዋታዎችን አሸንፈዋል ልንል እንችላለን። ነገር ግን የውድድር ዘመኑ ከመጀመሩ በፊት እኩል በሆነ ሁኔታ ውስጥ አልነበርንም። ምናልባት እኛም ደንቡን ብንጥስ ኖሮ ቡድኑን የተሻለ የሚያደርጉ ወይም ብዙ ጎል የሚያገቡ ተጫዋቾችን ልናስፈርም እንችል ነበር” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ቼልሲ ከ2009 እስከ 2022 ባለው ጊዜ ውስጥ ሶስት የሊግ ዋንጫዎችን፣ ሁለት የቻምፒዮንስ ሊግ፣ ሁለት የዩሮፓ ሊግ፣ አራት የኤፍ ኤ ካፕ እና አንድ የሊግ ካፕ አሸንፏል። በ2016-17 የውድድር ዘመን ሃዛርድ 16 ጎሎችን በማስቆጠር ለዋንጫው ድል ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ለቀረበላቸው ጥያቄ ፖቼቲኖ ሲመልሱ “ምናልባት አዎ” ብለዋል።
“ምንም ጥርጥር የለኝም፣ እውነቱን ለመናገርም አልፈራም። የቼልሲ ደጋፊዎች በእኔ ሊናደዱ ይችላሉ። ነገር ግን እኛም ቶተንሃም እያለን ደንብ ጥሰን ቢሆን ኖሮ ‘ደንብ ስለጣስን ዋንጫው አይገባንም’ ብዬ አመን ነበር። የተወሰኑ ክለቦች በኦፍሳይድ ህግ ሌሎቹ ደግሞ ያለ ኦፍሳይድ ህግ እንዲጫወቱ እንደማድረግ ነው፤ ይህ ደግሞ የማይቻል ነው። ለሁሉም እኩል ህግ ሊኖር ይገባል። ከዚያ በኋላ ነው ምርጥ ቡድን የመገንባት አቅምህ የሚመዘነው።”
“ቼልሲ ጥሩ አልተጫወተም ወይም ኮንቴ ጎበዝ አልነበረም እያልኩ አይደለም። መልእክቴ እንዲዛባብኝ አልፈልግም። ነገር ግን ደንብ ከጣስክ ዋንጫውን ለሌላ ቡድን መስጠት አለብህ። ለምን እንዲህ እንዳልተደረገ አላውቅም። አሁን እየተደረገ ያለው ነገር ደንብ መጣስን የሚያበረታታ ነው። ተገቢው ቅጣት ካልተላለፈ ‘በቶተንሃም ስራዬን ያጣሁት ዋንጫ ባለማሸነፌ ነው’ ማለቴ አይቀርም” ሲሉ አስተያየታቸውን ደምድመዋል።