ባሎገን የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ አስቀድሞ ዝውውሩ እንዲጠናቀቅ የሚያስችለውን ሰነድ ቢፈርምም፣ ብዙም ሳይቆይ ግን ውሳኔውን ቀይሯል። ኤቨርተን በአሜሪካዊው ኢንተርናሽናል የህክምና ምርመራ ላይ ችግር እንዳለ ከደረሰበት በኋላ እና ጆሹዋ ዚርክዚን ወይም ታሚ አብርሃምን በውሰት ለማስፈረም ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ሲቀር ከሞናኮ ጋር በክፍያ አወቃቀሩ ላይ ድጋሚ ድርድር አድርጎ ነበር።
የኤቨርተን ምንጮች የ25 ዓመቱ ተጫዋች ከፈረንሳይ የደረሰው ከታቀደው ሰዓት ዘግይቶ እንደሆነ እና ሞናኮ ተገቢውን የህክምና መረጃዎችን ለማጋራት በመዘግየቱ ችግሩን ለመፍታት ጊዜ እንዳጡ ገልጸዋል። ሆኖም ረቡዕ ዕለት በሞናኮ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ስኩሮ ዝውውሩ እንዲቋረጥ ያደረገው ኤቨርተን ለተጫዋቹ የሰጠው አያያዝ መሆኑን አጥብቀው ተናግረዋል።
“የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የወረቀት ስራዎችን ለማጠናቀቅ አንድ ተጨማሪ ሰዓት ለመጠየቅ የሚያስችል አሰራር አለው” ያሉት ስኩሮ፣ “ይህ የተደረገው የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ አምስት ደቂቃ ሲቀረው ነበር። እኔም ሆንኩ ኤቨርተን ውሉን ፈርመን ነበር። በመጨረሻው ሰዓት ግን ተጫዋቹ ላለመፈረም ወሰነ። ባሎገን ያቀረበው ምክንያት ‘ክለቡ እኔን በያዘበት መንገድ ደስተኛ አይደለሁም። የኤቨርተን የህክምና ክፍል ስለ ወደፊት ጤንነቴ ጥርጣሬ ያነሳበት መንገድ ምቾት አልሰጠኝም። ምንም አይነት የጤና ችግር የለብኝም፣ ስለዚህ እዚህ የረጅም ጊዜ ውል ለመፈረም አልፈልግም’ የሚል ነበር። የዝውውር መስኮታችንም በዚህ መልኩ ተጠናቀቀ” ብለዋል።
ስኩሮ ባልተሳኩት የዝውውር ጉዳዮች ከኤቨርተን ወይም ከቼልሲ ጋር “ጦርነት መክፈት” እንደማይፈልጉ ገልጸው፣ ኤቨርተን በባሎገን የህክምና ውጤት ላይ ያነሳውን ስጋት ግን ተቃውመዋል። “በአራት ሰዓት አካባቢ ባሎ ሊቨርፑል ውስጥ የህክምና ምርመራውን እያደረገ ነበር። ሁሉም ነገር በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነበር። በሰባት ሰዓት አካባቢ ግን ኤቨርተን ግንኙነት አድርጎ በባሎ የህክምና ውጤት ላይ ጥያቄዎችን አነሳ፣ ይህም ለኛም ሆነ ለተጫዋቹ የግል የህክምና ባለሙያዎች ምንም ትርጉም አልነበረውም። የቀረቡት ማብራሪያዎች የተጫዋቹን የወደፊት ሁኔታ አደጋ ላይ የሚጥሉ አልነበሩም።
“በሁለቱ ክለቦች የህክምና ክፍሎች መካከል ውይይት ተጀመረ። ኤቨርተን በጥልቀት ለመመርመር እና ከሌሎች ዶክተሮች ጋር ለመመካከር ሁለት ወይም ሶስት ሰዓታት ፈጅቶበታል፤ የክለብ ዶክተሮች ስጋት ሲያነሱ ይህ የተለመደ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ጉዳዩ በፍጥነት ወደ መገናኛ ብዙሃን ወጣ። እኛ ከተጠየቅን ከግማሽ ሰዓት በኋላ ባሎገን የህክምና ምርመራውን አላለፈም የሚል ወሬ ሚዲያ ላይ ወጥቶ ነበር። ከዚያም በእርግጥ ቼልሲ አጋጣሚውን ተጠቀመ።”
ቼልሲ ወደ ማንቸስተር ሲቲ የሚያመራውን ኤንዞ ፈርናንዴዝን ለመተካት ላሚን ካማራን በ47 ሚሊዮን ፓውንድ ለማስፈረም ተስማምቶ የነበረ ሲሆን የጽሁፍ ስምምነትም እንደነበረ ይታመናል። ይሁን እንጂ የገንዘብ ማሰባሰብ የፈለገው ሞናኮ፣ ባሎገንን መሸጥን ስለመረጠ ኤቨርተን በዝውውሩ ለመቀጠል ሲወስን ከቼልሲ ጋር የነበረውን ስምምነት ሰርዟል።
ስኩሮ ሲቀጥሉም “በኛ ሰዓት አቆጣጠር በአስር ሰዓት አካባቢ ኤቨርተን ምንም ችግር እንደሌለ ተረድቶ ‘ውሉን እንፈርም’ አለ። መረጃው እንደደረሰን ወደ ቼልሲ ተመልሰን ‘ሌላ ዝውውር ስላለን በላሚን ላይ ድርድር የለም’ አልናቸው። ይህን ማድረጉ ተገቢ ነው፣ የጨዋታውም አካል ነው። በዝውውር መስኮቱ የመጨረሻ ቀናት እንዲህ አይነት ሁኔታዎች ስለተፈጠሩ ሞናኮን እንደ መጥፎ አካል መቁጠር ትክክል አይደለም። በእግር ኳስ ኢንዱስትሪው ውስጥ ሁሉም ሰው ታማኝ እና ጥሩ ነው፣ ሞናኮ ብቻ ግን አይደለም የሚባለው ነገር አግባብ አይደለም” ብለዋል።
ሞናኮ በፈረንሳይ ያለውን የፋይናንስ ደንብ ለማሟላት ተጫዋቾችን የመሸጥ ግፊት ያለበት ሲሆን፣ የዝውውር መስኮቱ ክፍት ወደሆነባቸው አገራት ተጫዋቾችን አሳልፎ ሊሰጥ ይችላል። ስለ ካማራ የወደፊት ቆይታም ስኩሮ ሲናገሩ “በቅርቡ ትላንት ከቀረበለት የተሻሉ አማራጮች እና ጥያቄዎች እንደሚቀርቡለት ሙሉ እምነት አለኝ” ብለዋል።