የሲቲ እና የማድሪድ ጨዋታ አሸናፊ በሩብ ፍጻሜው ከአታላንታ ወይም ከባየር ሙኒክ አሸናፊ ጋር የሚገናኝ ሲሆን፣ ቼልሲ እና ሊቨርፑል በየመድባቸው ድል ካስመዘገቡ እርስ በርስ ሊገናኙ ይችላሉ። ኒውካስል እና ስፐርስም የየራሳቸውን የስፔን ተጋጣሚዎች ካሸነፉ የመገናኘት እድል አላቸው። አርሰናል ባየር ሌቨርኩሰንን ካሸነፈ በስምንቱ ውስጥ የቦዶ/ግሊምት እና የስፖርቲንግ ሊዝበን አሸናፊን ይገጥማል። የአርብ ዕለቱ ድልድል የግማሽ ፍጻሜ መንገዶችንም ያሳየ ሲሆን፣ ሁሉም የእንግሊዝ ክለቦች የሚገናኙበት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የመሆን ሰፊ እድልም ይታያል።
የቼልሲ እና የፒኤስጂ ጨዋታ በለንደኑ ክለብ በኤንዞ ማሬስካ እየተመራ 3 ለ 0 ያሸነፈበትን ባለፈው ክረምት የክለቦች ዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ትውስታ የሚቀሰቅስ ነው። የኒውካስል እና የባርሴሎና ጨዋታ በበኩሉ ሁለቱንም ክለቦች ያሰለጠኑትን የሰር ቦቢ ሮብሰንን ትውስታ የሚያድስ ሲሆን፣ ፋውስቲኖ አስፕሪላ እ.ኤ.አ በ1997 ባርሴሎና ላይ 3 ለ 2 ሲያሸንፉ ያስቆጠረውን ሶስት ግቦችም ያስታውሳል። ሁለቱ ቡድኖች በሴፕቴምበር ወር በሴንት ጀምስ ፓርክ የተገናኙ ሲሆን፣ በሃንሲ ፍሊክ የሚመራው ቡድን በማርከስ ራሽፎርድ ሁለት ግቦች 2 ለ 1 ማሸነፉ ይታወሳል። ሲቲ እና ማድሪድ በ13 ዓመታት ውስጥ በሻምፒዮንስ ሊግ የሁለት ዙር ጨዋታ ለስምንተኛ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል። የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎቹ በመጋቢት 10/11 እና 17/18 (እ.ኤ.አ) ይካሄዳሉ።