ኒውካስል ከጅምሩ ዝርክርክ የነበረ ሲሆን በቆመ ኳስም ተቀጥቷል። ጃራድ ብራንዝዌይት ከጄምስ ጋርነር የተሻማውን የማዕዘን ኳስ በግንባር በመግጨት ከመረብ አሳርፎታል። ኒውካስል ፒኤስቪ አይንድሆቨንን 3 ለ 0 ካሸነፈበት ጥር 21 ጀምሮ ባሉ 11 ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር አልወጣም። ኤዲ ሃው አንቶኒ ጎርደንን በአጥቂነት፣ 69 ሚሊዮን ፓውንድ የወጣበትን ጀርመናዊ አጥቂ ኒክ ዎልቴሜድን ደግሞ በመሀል ሜዳ በማሰለፍ ጀምረው ነበር። ነገር ግን ጎርደን በቀድሞ ክለቡ ላይ ተጽዕኖ መፍጠር ሲሳነው፣ አሰልጣኙ ዎልቴሜድን ወደ አጥቂነት ጎርደንን ደግሞ ወደ ግራ መስመር አዛውረዋል። ብዙም ሳይቆይ ኒውካስል በጃኮብ ራምሴ አማካኝነት አቻ መሆን ቻለ፤ ኳሷ በብራንዝዌይት ተረጭታ ፒክፎርድን አታላው ወደ ጎል ገብታለች።
የቀድሞው የሰንደርላንድ ግብ ጠባቂ ፒክፎርድ በቅዱስ ጄምስ ፓርክ ደጋፊዎች ዘንድ መዘበት የተለመደ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ የኒውካስል ደጋፊዎች ኒክ ፖፕን በእሱ ቢቀይሩ ደስተኞች እንደሚሆኑ ግልጽ ነው። የኒክ ፖፕ ስህተት ኤቨርተን መሪነቱን እንዲረከብ አስችሎታል። ግብ ጠባቂው ከድዋይት ማክኒል የተመታውን ኳስ በአግባቡ መያዝ ተስኖት ሲተፋው፣ ቤቶ ባገኘው አጋጣሚ ኳሷን ባዶ መረብ ላይ አሳርፏታል። በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ ራምሴ ሜዳው ላይ በተደጋጋሚ በማስታወኩ በጆ ዊሎክ ተቀይሮ መውጣቱ ለኒውካስል ሌላ መስተጓጎል ነበር። ብዙም ሳይቆይ ውጤታማ ያልነበሩት አንቶኒ ኢላንጋ እና ዎልቴሜድ በጃኮብ መርፊ እና ሃርቪ ባርነስ ተተኩ።
ቤቶ ከግብ ጠባቂ ጋር ብቻውን ተገናኝቶ ኳሱን ግብ አግዳሚው ላይ በመምታት ወርቃማ ዕድል አባክኗል። ቤቶ ተቀይሮ በቲየርኖ ባሪ ሲተካ፣ ዮአን ዊሳም ወደ ሜዳ ገብቷል። መርፊ በግሩም ሁኔታ ኳስን መትቶ ኒውካስልን አቻ ቢያደርግም፣ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ግን ባሪ ኤቨርተንን ዳግም መሪ አደረገ። ጎርደን ኳስ አሳልፎ መስጠቱን ተከትሎ ኪራን ዲውስበሪ-ሆል ያመቻቸውን ኳስ ባሪ ወደ ጎል ቀይሮታል። በመጨረሻም በጭማሪ ሰዓት ፒክፎርድ ለምን የእንግሊዝ አንደኛ ግብ ጠባቂ እንደሆነ ዳግም አሳይቷል። ቶናሊ በቮሊ የመታው ኳስ ግብ መሆኑ የማይቀር ቢመስልም፣ ፒክፎርድ ግን በሚገርም ብቃት ኳሷን አውጥቷታል።