League Table

ዌስትሃም በአርሰናል ጨዋታ የተሻረበትን ግብ በመቃወም ለዳኞች አካል ቅሬታ ሊያቀርብ ነው

ዌስትሃም ዩናይትድ በአርሰናል ላይ ያስቆጠረው ግብ ውድቅ መደረጉን ተከትሎ፣ ለፕሮፌሽናል ጌም ማች ኦፊሻልስ (PGMOL) ቅሬታውን ለማቅረብ ማቀዱ ተሰምቷል። ግቡ እንዲሻር የተደረገው ካለም ዊልሰን ኳሷን ከመረብ ከማሳረፉ በፊት ፓብሎ ፌሊፔ በግብ ጠባቂው ዴቪድ ራያ ላይ ጥፋት ፈፅሟል በሚል ነው። ይህ ውሳኔ በሊጉ የመቆየት ተስፋቸው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳደረባቸው ዌስትሃሞች፣ ፓብሎ ለምን እንደተቀጣ ግልፅ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ለዳኞች አካሉ ጥያቄ ለማቅረብ ተዘጋጅተዋል።

ክለቡ ቅሬታው የውጤት ለውጥ እንደማያመጣ ቢገነዘብም፣ በዋናው ዳኛ ክሪስ ካቫና እና በቪኤኤር (VAR) ዳኛው ዳረን ኢንግላንድ መካከል የተደረገውን የድምፅ ልውውጥ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። ካቫና በኢንግላንድ ምክር መሰረት ክስተቱን በሜዳ ዳር በሚገኘው ሞኒተር እንዲመለከት ተደርጎ ነበር። ግቡ ፀድቆ ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ቢጠናቀቅ ኖሮ ዌስትሃም 17ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቶተንሃም ጋር እኩል ነጥብ ይኖረው ነበር። ክለቡ በቆሙ ኳሶች ወቅት የሚፈፀሙ ጥፋቶች በዳኞች ዘንድ ወጥ የሆነ አተገባበር የላቸውም በሚል ከፍተኛ ቁጣውን ገልጿል።

በሌላ በኩል በርካታ የቀድሞ ዳኞች ካቫና እና ኢንግላንድ ያስተላለፉት ውሳኔ ትክክል መሆኑን እየገለፁ ይገኛሉ። የእግር ኳስ ህግ አውጪው አካል (IFAB) ከመጪው መኸር ጀምሮ በሚያደርገው ውይይት፣ በቆሙ ኳሶች ወቅት የሚታየውን መተናነቅ እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል። የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በበኩላቸው በዌስትሃም የተሰጠው ውሳኔ “ግባቸውን ለማሳካት ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ በሚል ትግል ላይ ያሉ የሁለት ታላላቅ ክለቦችን ታሪክ” ሊወስን እንደሚችል ገልፀው፣ ዳኞቹን “በጣም ደፋሮች” ሲሉ አሞካሽተዋል።