League Table

“ነገሮች ሰዎች እንደሚመስላቸው አይደሉም”፦ ሮሲኒየር የኤንዞ ፈርናንዴዝን ውዝግብ ለማርገብ ጥረት እያደረጉ ነው

ሊያም ሮሲኒየር ከኤንዞ ፈርናንዴዝ ጋር “በጣም ጥሩ ሁኔታ” ላይ መሆናቸውን በመግለጽ፣ የቼልሲው ምክትል አምበል በብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ወቅት በሰጠው አስተያየት የተቀሰቀሰውን ውዝግብ ለማርገብ ጥረት አድርገዋል። ፈርናንዴዝ ስለ ቀድሞዎቹ የሪያል ማድሪድ አማካዮች ቶኒ ክሮስ እና ሉካ ሞድሪች በከፍተኛ አድናቆት መናገሩ፣ እንዲሁም ማድሪድ በአውሮፓ ለመኖር የሚመርጣት ከተማ መሆኗን መጥቀሱ በቼልሲ ቆይታው ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር አድርጎ ነበር።

ወደ ሪያል ማድሪድ ሊዛወር እንደሚችል የሚነገርለት ፈርናንዴዝ፣ በመጋቢት 17 በሻምፒዮንስ ሊግ የ16ቱ ዙር ሁለተኛ ጨዋታ ቼልሲ በፓሪስ ሴንት ዠርሜን ከተሸነፈ በኋላ፣ ስለ ቼልሲ የወደፊት ቆይታው በክረምቱ ከሚካሄደው የዓለም ዋንጫ በኋላ እንደሚወስን መናገሩ ይታወሳል። ሮሲኒየር የፈርናንዴዝ የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች “መስመር ያለፉ” እና እየገነቡት ያለውን የቡድን ባህል አደጋ ላይ የሚጥሉ እንደሆኑ በማመናቸው፣ ተጫዋቹ ቅዳሜ ቡድኑ ፖርት ቫሌን 7 ለ 0 ባሸነፈበት የኤፍኤ ካፕ ሩብ ፍፃሜ እና በሚቀጥለው እሁድ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በሚደረገው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ላይ እንዳይሰለፍ አግደውታል።

ሆኖም የቼልሲው አሰልጣኝ ፈርናንዴዝ በስታምፎርድ ብሪጅ ተገኝቶ የፖርት ቫሌን ጨዋታ በመመልከቱ መደሰታቸውን ገልጸው፣ ጉዳዩን ለመዝጋት እንደሚፈልጉ አመልክተዋል። ሮሲኒየር ሲናገሩ “በትክክለኛው ጊዜ እና ሁኔታ፣ አሁን ባሳለፍነው ሂደት ውስጥ በእኔ እና በኤንዞ መካከል ስለተባሉት ነገሮች ውይይት እንደሚደረግ እርግጠኛ ነኝ። ኤንዞ እና እኔ በጣም ጥሩ በሆነ ሁኔታ ላይ እንገኛለን። ዛሬ አይቼዋለሁ፣ ፊት ለፊትም በጣም ጥሩ ውይይት አድርገናል፤ ነገሮችም ሰዎች እንደሚመስላቸው ላይሆኑ ይችላሉ” ብለዋል።

አሰልጣኙ አክለውም “አርብ ዕለት እንደተናገርኩት… ከእያንዳንዱ ተጫዋች፣ ከኤንዞም ሆነ ከማንኛውም የቡድኑ አባል ጋር እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይ የማደርገው ንግግር በውስጥ የሚቀር ነው። የመልበሻ ክፍል ክብር ሊጠበቅ ይገባል። ስለ እሱ እንደ ሰው ያለኝን አመለካከት አርብ ዕለት በግልፅ ተናግሬያለሁ። እሱ በጣም ምርጥ ሰው ነው። አሁን ግን ትኩረታችን በኳሱ ላይ እንዲሆን እና በዚህ የውድድር ዘመን ማሳካት የምንፈልገውን እንድናሳካ እፈልጋለሁ” ብለዋል።

የሮሲኒየር የቅጣት ውሳኔ በተጫዋቹ ወኪል በኩል ደስ የማይል ምላሽ አስከትሏል። ጃቪየር ፓስቶሬ ውሳኔው “ፍጹም ኢ-ፍትሃዊ” መሆኑን እና ፈርናንዴዝ ቼልሲን የመናቅ ፍላጎት እንዳልነበረው ገልጿል። ሮሲኒየር ለፓስቶሬ በሰጡት ምላሽ “ያ የእሱ አመለካከት ነው። በሌላ ሰው አመለካከት ላይ የምለው ነገር የለም። ኤንዞ ስለ እሱ የማስበውን ያውቃል፤ ተጫዋቾቹን ለመደገፍ እዚህ መገኘቱም በጣም ጥሩ ነበር። ወደፊት እንጓዛለን፣ በውድድር ዘመኑ ማጠናቀቂያ ላይም ጥሩ ውጤት እንደምናመጣ እናረጋግጣለን” ብለዋል።

ክንፍ ተጫዋቹ ጄሚ ጊተንስ አርብ ዕለት በልምምድ ወቅት ሌላ የጅማት (hamstring) ጉዳት እንደደረሰበት የገለጹት ሮሲኒየር፣ ተጫዋቾቻቸው በፖርት ቫሌው ጨዋታ ባሳዩት ትጋት እና ጥንካሬ መደሰታቸውን ገልጸዋል። “እንደ እኔ ሁሉ የኤፍኤ ካፕን በማሸነፍ እና ለሻምፒዮንስ ሊግ በማለፍ ረገድ ድንቅ የውድድር ዘመን ማሳለፍ እንደምንችል የሚያምኑ ተጫዋቾች አሉኝ” ሲሉ ንግግራቸውን አጠቃለዋል።