ይህ የ22 ዓመቱ ተጫዋች ከተቀያሪ ወንበር ተነስቶ ግብ ያስቆጠረባቸው ባለፉት አራት ጨዋታዎች ለሶስተኛ ጊዜ ነው። ከሁለት ሳምንት በፊት በዌስትሃም ዩናይትድ 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት በተጠናቀቀው ጨዋታ በ96ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ ያስቆጠረ ሲሆን፣ የካቲት 1 ቀን ደግሞ ፉልሃምን 3 ለ 2 ባሸነፉበት ጨዋታ በ93ኛው ደቂቃ ላይ የማሸነፊያ ግብ ማስቆጠሩ ይታወሳል።
“በቋሚነት መሰለፍ አለብኝ ብዬ ጭራሽ አላስብም። ለእኔ ዋናው ነገር አሰልጣኙ በሚፈልግበት ጊዜ ሁሉ ዝግጁ ሆኖ መገኘት ነው” ሲል ሴስኮ ተናግሯል። “አምስት ደቂቃም ቢሰጠኝ በዚያች አጭር ጊዜ ውስጥ ቡድኑን ለመርዳትና በጨዋታው ለመደሰት እሞክራለሁ። በእርግጥ ስለ ቋሚ ተሰላፊነት እናወራለን፤ ማይክል ካሪክ እና ሌሎችም በኔ ላይ እምነት አላቸው። በቅርቡ በቋሚነት እንድሰለፍ እያዘጋጁኝ ነው፤ ነገር ግን ዋናው ትኩረቴ በምሰጠው ደቂቃ ሁሉ ቡድኑን ውጤታማ ማድረግና ድል እንዲቀናን መርዳት ላይ ነው።”
ሴስኮ የማንቸስተር ዩናይትድ አጥቂ መሆን የሚያስከትለውን ጫናም በአዎንታዊ መልኩ እንደሚመለከተው ገልጿል። “ጫናን እንደ ትልቅ ዕድል ነው የምመለከተው። ጥሩ ተጫዋች መሆን ከፈለግኩ ሊኖር የሚገባ ነገር ነው። ከፍተኛ ደረጃ ላይ መጫወት የሚፈልግ ተጫዋች ይህንን መቀበል አለበት፤ በእኔ ላይ ምንም የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ የለም” ብሏል ስሎቪኒያዊው አጥቂ።
ዩናይትድ በማይክል ካሪክ ጊዜያዊ አሰልጣኝነት ስር ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ከሚቻለው 18 ነጥብ 16ቱን ሰብስቧል። “በቡድኑ ውስጥ ያለው መንፈስ በጣም ጥሩ ነው” ሲል ሴስኮ ተናግሯል። “ሁሉም ለሌላው ይሰራል። ካሪክ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ረዳቶቹም ድንቅ ናቸው። በእያንዳንዱ ተጫዋች ላይ በዝርዝር የሚሰሩት ስራ ውጤታማ እንድንሆንና ብዙ ነጥቦችን እንድንሰበስብ ረድቶናል” ሲል አክሏል።
በሌላ በኩል የኤቨርተኑ ተከላካይ ጃራድ ብራንዝዌይት በዚህ የውድድር ዘመን በፕሪሚየር ሊጉ ሶስት ጨዋታዎችን ብቻ በቋሚነት ቢጀምርም፣ ለእንግሊዝ የዓለም ዋንጫ ስብስብ ውስጥ ለመካተት ተስፋ አልቆረጠም። የ23 ዓመቱ ተከላካይ በጉልበት ጉዳት ምክንያት የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ አጋማሽ ያመለጠው ሲሆን፣ አዲሱ የእንግሊዝ አሰልጣኝ ቶማስ ቱሄልም ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ስብስቦች ውስጥ አላካተቱትም ነበር።
ይሁን እንጂ በዴቪድ ሞይስ ስር ወደ ሜዳ ተመልሶ ሰኞ ዕለት ከዩናይትድ ጋር በነበረው ጨዋታ በግራ ተከላካይነት የተሰለፈው ብራንዝዌይት፣ ለበጋው ውድድር ጥሪ ይደርሰኛል የሚል እምነት አለው። “ጉዳቱ በነበረኝ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ አሳድሮብኛል፤ አሁን ግን ከጉዳት ነፃ ሆኜ ለዓለም ዋንጫው ስብስብ ራሴን ለማዘጋጀት እጥራለሁ” ብሏል። ቱሄል የዓለም ዋንጫ ስብስባቸውን ከመሰየማቸው በፊት በመጋቢት ወር ከኡራጓይ እና ጃፓን ጋር የሚደረጉ የወዳጅነት ጨዋታዎች አሏቸው። ብራንዝዌይት ለረጅም ጊዜ ከሜዳ መራቁ፣ ብዙ ጨዋታ ካደረጉ ተጫዋቾች በተሻለ “ትኩስ ጉልበት” ይዞ እንዲመጣ ሊረዳው እንደሚችልና በዓለም ዋንጫ መጫወት ህልሙ እንደሆነ ገልጿል።