የስፐርሱ ተከላካይ ሚኪ ቫን ደ ቬን ክለቡ እስከ መጨረሻው ድረስ እንዲጨነቅ መደረጉ “አሳፋሪ” መሆኑን ቢናገርም፣ በመጨረሻ ግን የእፎይታ እና የደስታ ቀን ሆኖ አልፏል። ዴ ዜርቢ ሲናገሩም “ይህ በቆይታዬ ካስመዘገብኳቸው ስኬቶች ሁሉ ትልቁ ነው ብዬ አስባለሁ። ከብራይተን ጋር ወደ ዩሮፓ ሊግ መግባት ትልቅ ነበር። በማርሴይ ከብዙ ችግሮች ጋር ሁለተኛ መውጣትም ትልቅ ስኬት ነበር። ነገር ግን የዛሬው ቀን እስካሁን በእግር ኳስ ካሳለፍኳቸው ምርጥ ቀናት አንዱ ይመስለኛል” ብለዋል።
አሰልጣኙ አክለውም “በእርግጥ ከስህተቶቻችን መማር አለብን። በሊጉ በመቆየታችን ደስተኞች ነን፣ ያለፈውንም እንረሳዋለን። እንዲያውም አይ! ሞኞች ናቸው ያለፈውን የሚረሱት። ብልህ እና ዋጋ ያላቸው ሰዎች ያለፈውን ሊረሱ አይችሉም፣ ሁልጊዜም በአእምሯቸው ይይዙታል። ከስህተቶቻችን መሻሻል አለብን። ከዛሬ ምሽት ጀምሮ፣ ከነገ ጀምሮ ቡድኑን እንደገና መገንባት ለመጀመር በጉጉት እንጠባበቃለን። ለእረፍት የምንሄድበት ጊዜ የለንም” ሲሉ ገልጸዋል።
“በዚህ ይጠነክራሉ ወይ?” ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም “ይህን ቀን ካስታወስን በእርግጥ እንጠነክራለን። በሚቀጥለው የውድድር ዘመን፣ በእያንዳንዱ የልምምድ ክፍለ ጊዜ ምርጣችንን ለመስጠት የሆነውን ነገር በአእምሯችን መያዝ አለብን። ይህን ካስታወስን ነገሮች ቀላል ይሆኑልናል” ብለዋል። ዴ ዜርቢ ለስፐርስ ወሳኝ ስለሚሆነው የበጋ የዝውውር ወቅትም ሲናገሩ “ብዙ ተጫዋቾችን መቀየር የለብንም። ሊቆዩ የሚችሉ ብቁ የሆኑ 10፣ 11፣ 12 ተጫዋቾች አሉን – እንደ ተጫዋችም ሆነ በተለይ እንደ ሰው ጥሩ የሆኑ። ከዚያ በኋላ በጣም ስለተሰቃየን ቡድኑን በከፍተኛ ደረጃ ተጫዋቾች ማሟላት አለብን” ብለዋል።
ዴ ዜርቢ አክለውም “እኛ ቶተንሃም ነን፣ በሊጉ ለመቆየት እስከ መጨረሻው ጨዋታ የመጨረሻ ሰከንድ ድረስ እንዲህ መሰቃየት የለብንም። አሁን በሊጉ የመቆየት ግቤ ተሳክቷል። ቀጣዩ ግቤ በህልሜ እና በአእምሮዬ ካለው ቡድን ጋር የቅድመ ውድድር ዝግጅት መጀመር ነው” ብለዋል። ቫን ደ ቬን በበኩሉ “በዚህ የውድድር ዘመን ያደረግነው የመጨረሻ ጨዋታ ከወርጅት ለመትረፍ መሆኑ ተቀባይነት የለውም። ይህ ክለብ ድንቅ ተጫዋቾች አሉት። እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ እንዲቆይ ማድረጋችን አሳፋሪ ነበር፣ ነገር ግን ማድረግ ችለናል፣ ዋናው ነገርም ይሄ ነው። በመጨረሻ ላይ በጣም በስሜት ተውጬ ነበር። በግሌም ቢሆን አስቸጋሪ የውድድር ዘመን ነበር። ሁሉንም ጨዋታዎች ማለት ይቻላል ተጫውቻለሁ እናም ብዙ ተሰቃይቻለሁ። አሁን በጣም ደስተኛ ነኝ፣ ይህ ደግሞ ዳግም እንዲከሰት መፍቀድ የለብንም” ሲል ተናግሯል።