የማንቸስተር ዩናይትድ ስብስብ ከተለያዩ ማህበረሰቦች የተውጣጡ ተጫዋቾችን የያዘ ሲሆን፣ ካሪክ አርብ ዕለት በሰጠው መግለጫ ራትክሊፍ በይፋ ከጠየቁት ይቅርታ በተጨማሪ ለጊዜያዊ አሰልጣኙ እና ለተጫዋቾቹ በግል ያቀረቡት ይቅርታ ወይም ማብራሪያ መኖሩ ተጠይቆ ነበር። “ጂምን ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት በአርሰናሉ ጨዋታ ወቅት ነበር፣ በዚህም ደስተኛ ነኝ” ሲል ጥር 17 (ጃንዋሪ 25) በሜዳቸው ውጭ ስላሸነፉበት ጨዋታ ተናግሯል። “ለእኔ የስራ ድርሻ ከበላይ አካላት ጋር የማያቋርጥ ግንኙነት ማድረግ አስፈላጊ ነው ብዬ አላስብም። የእኔ ስራ በቡድኑ ውስጥ ምቹ ሁኔታን መፍጠር እና የመጀመሪያውን ቡድን መምራት ነው። አሁን እዚህ ተቀምጬ ለደጋፊዎች የምሰጠው መግለጫ የሥራዬ አካል ነው፤ ነገር ግን ከበላይ አካላት የማያቋርጥ ግንኙነት የግድ አያስፈልገኝም” ብሏል።
ሰኞ ምሽት ከኤቨርተን ጋር የሚጋጠመው የካሪክ ቡድን፣ ራትክሊፍ በሰር አሌክስ ፈርጉሰን ዘመን የተገነባውን የክለቡን የአንድነት መንፈስ አላዳከሙትም ወይ ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ፤ “በእርግጥም ሁላችንም በአንድነት እየሰራን ነው” ሲል ምላሽ ሰጥቷል። “ባለፉት ጥቂት ሳምንታት እዚህ በመገኘቴ እና በስታዲየሞች ውስጥ በነበረኝ ቆይታ፣ እንደ አንድ ቡድን በጠንካራ ሁኔታ እየተንቀሳቀስን መሆኑ ግልጽ ነው” ብሏል።
ካሪክ ጥር 5 (ጃንዋሪ 13) ሩበን አሞሪምን ተክቶ ስራ ከጀመረ ወዲህ፣ በየካቲት 7 (ፌብሩዋሪ 14) ከ18 ዓመት በታች ቡድን ማንቸስተር ሲቲን 3-1 ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ ጨምሮ የአካዳሚ ጨዋታዎችን ሲከታተል ቆይቷል። ይህ ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ሲያስረዳ በዌስትሃም ወጣት ተጫዋች በነበረበት ወቅት የ1998-99 የኤፍኤ ወጣቶች ዋንጫን ያሸነፈበትን ትዝታ ጠቅሷል። “ይህ ከማደጌ ጋር የተያያዘ ነው” ብሏል። “በዌስትሃም በነበርኩበት ጊዜ ሃሪ ሬድናፕ አሰልጣኝ፣ ፍራንክ ላምፓርድ ሲኒየር ደግሞ ረዳት አሰልጣኝ ነበሩ። ትልቁ ትኩረት ወደ ዋናው ቡድን የሚያደርስ መንገድ መፍጠር እና ከዋናው ቡድን ጋር ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ ነበር።”
“ከዋና ዋና ተሞክሮዎቼ አንዱ በወጣቶች ዋንጫ መጫወቴ ነበር። ከዮርክ ጋር ከለንደን ራቅ ባለ ቦታ ማክሰኞ ምሽት እንጫወት ነበር፤ ፍራንክ ላምፓርድ ሲኒየር መጥቶ ጨዋታውን ተመልክቶናል። ያንን ከብዙ ዓመታት በኋላ አሁንም አስታውሰዋለሁ፤ በዚያ ምሽት ፍጹም ቅጣት ምት ስቼ ነበር። ወደዚህ ክለብ ስንመጣ እንዲህ ያለው ግንኙነት፣ ስኬታችን፣ ታሪካችን እና ወጋችን እኔ በከፍተኛ ፍላጎት የምሰራበት ጉዳይ ነው። ተጫዋቾች በስርዓቱ ውስጥ አልፈው ወደ ዋናው ቡድን እንዲቀላቀሉ እና የዚያ አካል እንዲሆኑ እንፈልጋለን” ሲል ንግግሩን አጠቃሏል።