በዚህ ወቅት የዩናይትድ ወቅታዊ አቋም በሊጉ ከማንኛውም ቡድን የተሻለ ቢሆንም፣ አንድ ቀሪ ጨዋታ እያላቸው ከአርሰናል በ13 ነጥብ ዘግይተው ይገኛሉ። ዩናይትድ ረቡዕ እለት ከኒውካስል ጋር ከሚያደርገው ጨዋታ በፊት፣ ካሪክ የሚኬል አርቴታን ቡድን የመድረስ ተስፋ እንዳላቸው ተጠይቀው ነበር። “በእግር ኳስ ማንኛውንም ነገር ወደ ጎን ማለት አይቻልም” ያሉት ካሪክ፣ “ነገር ግን ተጨባጭ መሆንና ያለንበትን ደረጃ ማወቅ አለብን። ጨዋታዎችን ማሸነፍ መቀጠልና ውጤቱን ማየት ያለብን ይመስለኛል። ከእኛ በላይ ሁለት ድንቅ ቡድኖች አሉ። በዙሪያችንም በጣም ጥሩ ቡድኖች አሉ። ጥሩ ጉዞ እያደረግን ነው፣ ሆኖም በትዕቢት አንወጠርም። ታጋሽ መሆንና በወቅቱ ያለውን ሁኔታ መረዳት፣ እንዲሁም በራስ መተማመንን መውሰድ ያስፈልጋል። ይህ የት እንደሚያደርሰን ወደፊት እናየዋለን፣ ነገር ግን ጥረታችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።
ካሪክ በዩናይትድ አማካይ በነበሩበት ወቅት በሰር አሌክስ ፈርጉሰን ስር አምስት የሊግ ዋንጫዎችን አንስተዋል። የስኮትላንዳዊው አሰልጣኝ ጠንካራ ተወዳዳሪነት ለዋንጫው ተስፋ መነሳሻ ሊሆን እንደሚችል ለካሪክ ቀርቦላቸዋል። ካሪክ ሲመልሱ “ከአሉታዊ ጎኑ ይልቅ ሊሳኩ በሚችሉ ነገሮች ላይ ‘ብርጭቆው በግማሽ ሞልቷል’ ብዬ እንደማስብ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ” ብለዋል። “በእርግጥ ተጨባጭ እየሆንኩ ነው – ያ እንዲሆን ብዙ ጨዋታዎችን ማሸነፍ አለብን። ስለዚህ እያደረግን ያለነውን እንቀጥላለን፣ በየተራ እያንዳንዱን ጨዋታ እናያለን። አሁን አንድ ጨዋታ አለን፣ ከዚያም ከአስቶን ቪላ ጨዋታ በፊት ትንሽ እረፍት እናገኛለን፣ ስለዚህ ረቡዕ ምሽት ያለንን ሁሉ እንሰጣለን” ሲሉ አክለዋል።
እስከ የውድድር ዘመኑ መጨረሻ ኮንትራት ያላቸው ካሪክ፣ ቡድኑ ስኬታማነቱን ከቀጠለ ቋሚ አሰልጣኝ የመሆን እድላቸው ሰፊ መሆኑን ስለመቀበላቸው ተጠይቀው ነበር። “እውነቱን ለመናገር በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ የምለው የለም” ብለዋል። “እዚህ በመሆኔ ደስተኛ ነኝ። የምሰራውን ስራም እወደዋለሁ። ከመጀመሪያው ጀምሮ እንደተናገርኩት፣ ለአጭር ጊዜ ወይም ለጊዜያዊ መፍትሄ ብዬ የምወስነው ውሳኔ የለም። እዚህ ለምን ያህል ጊዜም ብቆይ፣ ለክለቡ የረጅም ጊዜ ጥቅም የሚበጁ ውሳኔዎችን የማሳለፍ ኃላፊነት እንዳለብኝ አምናለሁ። በእርግጥ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ይረዳል፣ ልጆቹም በዚህ ረገድ ጥሩ እየሰሩ ነው። መጨረሻው ምን እንደሚሆን እናያለን” ብለዋል።
ኒውካስል በ15 ነጥብ ዝቅ ብለው የሚገኙ ሲሆን ያለፉትን ሶስት የሜዳቸው ጨዋታዎች ተሸንፈዋል። ሆኖም ካሪክ “እዚያ መጫወት ፈታኝ ነው። ደጋፊዎቻቸው ባሉበት ሜዳቸው ላይ ጠንካራ ቡድን ስለሚሆኑ ለዚያ ዝግጁ መሆን አለብን” ብለዋል። በጉዳት በኩል ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ እና ሜሰን ማውንት አሁንም ከሜዳ የራቁ ሲሆን፣ በፓላሱ ጨዋታ ህመም ተሰምቷቸው የወጡት ሃሪ ማጓየር እና ሉክ ሾው የጤና ምርመራ ይደረግላቸዋል።