የአርሰናሉ አሰልጣኝ “በጣም አስቸጋሪ በሆነ ቦታ ላይ ጠንካራ ተጋጣሚን ማሸነፍ ነበረብን” ብሏል። “ሳንደርላንድ የመተንፈሻ ቀዳዳ ሊያሳጣህ ይችላል፤ በጣም አካላዊ ጉልበት የሚጠይቅና ቀጥተኛ አጨዋወትን መርጠዋል፤ እኛ ደግሞ በእኔ እይታ በዚህ የውድድር ደረጃ ተቀባይነት የሌለውን ሁኔታ ማለፍ ነበረብን። በጣም አዝኛለሁ፣ ተጨንቄአለሁም፤ ምክንያቱም ይህ በምንም ተአምር የፍጹም ቅጣት ምት ሊሆን አይገባውም ነበር። ይህ ከተጋጣሚው የተሰነዘረ የጁዶ ውርወራ ነው። ኤዝሪ ያደረገው ምንም ነገር የለም። ጨዋታውን የመጠበቅ ኃላፊነት አለብን። ዛሬ ጨዋታው ጥበቃ አልተደረገለትም፤ ይህም ድላችንን እና ግስጋሴያችንን ሊያሳጣን ይችል ነበር። በእውነት አዝኛለሁ፣ ይህ መከሰት አልነበረበትም” ሲል ቅሬታውን ገልጿል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ከአሰልጣኞች ክልል ደጋግሞ በመውጣቱ ቢጫ ካርድ የተመለከተው አርቴታ የጊማሬሽን ግብ “ቆንጆ” ሲል አወድሷል። ቡካዮ ሳካ በጭማሪ ሰዓት ላይ ሁለተኛውን ግብ በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠረ ሲሆን፥ የሳንደርላንዱ ሬይኒልዶ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። የሳንደርላንዱ አሰልጣኝ ለ ብሪስ በበኩላቸው የተደበላለቀ ስሜት እንደተሰማቸው ገልጸዋል። “በአሁኑ ሰዓት በአእምሮዬ ያሉት ሁለት ቃላት ኩራት እና ብስጭት ናቸው” ብለዋል። “በአሁኑ ሰዓት በአውሮፓ ካሉ ምርጥ ቡድኖች አንዱ በሆነው ክለብ ላይ ትልቅ ነገር ለማሳካት ምን ያህል እንደተቃረብን ስላሳየን ኮርቻለሁ። ከመጀመሪያው አጋማሽ በኋላ በኳስ ቁጥጥሩ ላይ ጥንቃቄ አብዝተን ነበር፤ ነገር ግን ሁለተኛው አጋማሻችን ድንቅ ነበር።”
አሰልጣኙ በመቀጠል “ጫና መፍጠር ችለን ነበር፣ እድሎችንም አግኝተናል፤ የራያ የፍጹም ቅጣት ምት መከላከልም ትልቅ ነበር። እኔ እንደማስበው የፍጹም ቅጣት ምቱ መጥፎ ከመሆኑ ይልቅ የግብ ጠባቂው ብቃት አስደናቂ ነበር። ራያ ዛሬ በእውነት የሚደነቅ ነበር። በጨዋታው ውስጥ መቆየት ችለን ነበር፣ ሌሎች እድሎችንም ፈጥረን ነበር ነገር ግን ግብ አላስቆጠርንም፤ የዛሬው ልዩነትም ይሄ ነበር። ከፍተኛ ጥረት እና አንድነት ነበረን፤ አልፎ አልፎም በኳስ ቁጥጥሩ ላይ ደፋር ነበርን። ይህ አርሰናል እድሎችን የሚፈጥር ቡድን በመሆኑ በታክቲክ ተለዋዋጭ መሆን ነበረብን። ዛሬ እነሱን ለማቆም መፍትሄ አግኝተናል፣ እኛም እድሎችን ፈጥረናል፤ ይህም እየተሻሻልን መሆኑን ያሳያል። ገና በቂ ባይሆንም ተቃርበናል” ብለዋል።