የሊቨርፑሉ አማካይ ከርቲስ ጆንስ የኮንትራት ዘመኑ የመጨረሻ 12 ወራት ውስጥ በሚገባበት በሚቀጥለው ክረምት፣ ኢንተር ሚላን ተጫዋቹን ለማስፈረም ያለውን ፍላጎት ዳግም ያድሳል ተብሎ ይጠበቃል። ጆንስ ከልጅነት ክለቡ ጋር አዲስ ውል ለመፈረም ላለፉት ጥቂት ወራት ንግግር ሲያደርግ ቢቆይም፣ እስካሁን ድረስ በስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም።
በጥር ወር የዝውውር መስኮት የ25 ዓመቱን ተጫዋች ሁኔታ የጠየቁት የጣሊያን ሻምፒዮናዎቹ፣ አሁንም ለእንግሊዛዊው ኢንተርናሽናል ያላቸው ፍላጎት አልቀነሰም። በዚህም ምክንያት በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሌላ ጥያቄ ማቅረባቸው አይቀርም። ሊቨርፑል እንደ ተጫዋቹ ዕድሜ እና ብቃት ጆንስን በ35 ሚሊዮን ፓውንድ ይገምተዋል። ሆኖም በ2027 በነፃ ሊገኝ ለሚችል ተጫዋች ኢንተር ይህን ያህል ገንዘብ ይከፍላል ወይ የሚለው ገና የሚታይ ይሆናል።
ጆንስ በአርኔ ስሎት የመሃል ሜዳ ክፍል ውስጥ ቋሚ የመሰለፍ እድል ለማግኘት እየታገለ ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ እንደ አስቸኳይ ጊዜ የቀኝ መስመር ተከላካይ ሆኖ ተሰልፎ ተጫውቷል። የሊቨርፑል ደጋፊ ሆኖ ያደገው ይህ ተጫዋች፣ መሐመድ ሳላህ ቅዳሜ ዕለት የቡድኑን የአጨዋወት ዘይቤ በመንቀፍ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋራው ጽሁፍ ላይ ‘ላይክ’ ካደረጉት በርካታ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበር።