ይህ የዋንጫ ብዛት የታላቅነቱ ማሳያ እንደሆነ ለጋርዲዮላ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር። እርሱም ሲመልስ ሲቲ ያሸነፋቸውን ሁለት የኮምዩኒቲ ሺልድ ድሎች በመጥቀስ በቀኝ ክንዱ ጡንቻውን በፈገግታ እያሳየ፣ “አዎ፣ በ10 አመት ውስጥ 19 ዋንጫዎች ማግኘት መጥፎ አይደለም” ብሏል። በመቀጠልም በሲቲ ያስመዘገበው ስኬት በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ እንደ ተራ ነገር መታየቱ ተጠይቆ ነበር። እርሱም ሲመልስ “እስከምሄድ መጠበቅ አያስፈልጋቸውም፣ እዚህ በነበርኩበት ጊዜ ሁሉ ነገሮች አስደሳች እንደነበሩ ያውቃሉ። በጣም አስደሳች ነበር። ስለዚህ በ10 አመት ውስጥ 19 ዋንጫዎችን ማግኘት እና ለ20ኛው መታገል በእውነት መጥፎ አይደለም” ብሏል።
ጋርዲዮላ በሚቀጥለው ወር የሚለቅ ከሆነ የዌምብሌይ ጉብኝቱ በሀዘን የታጀበ ሊሆን ይችላል ወይ ተብሎ ተጠይቆ ነበር። “በፍጹም፣ በፍጹም፤ ገና የአንድ አመት ኮንትራት ይቀረኛል” ብሏል። “በዌምብሌይ ለኔ የሚሆን ቋሚ ቦታ ባለመዘጋጀቱ ቅር ብሎኛል፤ እዚያ በሄድኩበት ቁጥር ቢያንስ አንድ ላውንጅ ወይም ቦክስ ሊሰጡኝ ይገባ ነበር። ምናልባት ሌላ 24 ጊዜ ልሄድ እችላለሁ” ሲል በቀልድ መልክ ተናግሯል።
“ዌምብሌይ ለኔ ልዩ ቦታ ነው፤ እ.ኤ.አ. በ1992 ከባርሴሎና ጋር እንደ ተጫዋች የአውሮፓ ዋንጫን በማሸነፍ፣ ከዚያም በ2011 ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር እንደ ዋና አሰልጣኝ ሻምፒዮንስ ሊግን በማሸነፍ እና እዚህ ከመጣሁ በኋላም ለብዙ የግማሽ ፍጻሜ እና የፍጻሜ ጨዋታዎች ተገኝቻለሁ። ወደ ዌምብሌይ ዳግም መመለስ በጣም ጥሩ ነው። ድንቅ ነው።” ሲል አክሏል። አማካዩ ሮድሪ ዛሬ ቼልሲን ለመግጠም የሚያስችል ብቃት ላይ ስለመሆኑ የጤና ምርመራ ይደረግለታል።