የኪሊያን ምባፔ፣ ሊዮኔል ሜሲ እና ኔይማር የፊት መስመር ጥምረት በጣም አስደሳች ቢመስልም፣ ፓሪስ ሴንት ዠርሜንን ለቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ማቅረብ አልቻሉም ነበር፤ በስራቸውም ውስጥ ደስታ አይታይባቸውም ነበር። ማጥቃት ላይ ብቻ ማተኮር እና አለመከላከል ፒኤስጂን አሰልቺ ቡድን አድርጎት ቆይቷል። በውድቀታቸው ውስጥ አንድ ትልቅ ትምህርት ነበረ፦ እግር ኳስ ተቀይሯል፣ ጨዋታዎችንም በአጥቂዎች ብቃት ብቻ ማሸነፍ አይቻልም።
ሉዊስ ኤንሪኬ ይህንን ትምህርት ለምባፔ በክለቡ በነበረው የመጨረሻ አመት ሊያስተምረው ሞክሯል። በአሰልጣኙ የመጀመሪያ አመት ላይ በተሰራው ዘጋቢ ፊልም ላይ፣ ምባፔ እንደ ጥፋተኛ ተማሪ ተቀምጦ ከባርሴሎና ጋር በነበረው የቻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ላይ የነበረበትን የመከላከል ድክመት እንዲመለከት የተደረገበት ትዕይንት ነበር። ኤንሪኬ ፍላጎቱን በግልፅ አስቀምጦ ነበር፦ “ማይክል ጆርዳንን እንደምትወድ አንብቤአለሁ” አለው። “ማይክል ጆርዳን የቡድን አጋሮቹን በቁጥጥሩ ስር አድርጎ እንደ እብድ ይከላከል ነበር። አንተ ለኛ ግብ ብቻ ማስቆጠር ያለብህ ይመስልሃል። አዎ፣ አንተ ድንቅ እና አለም አቀፍ ተጫዋች ነህ፣ በዚህ ጥርጥር የለውም፤ ነገር ግን ያ ለእኔ ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም። መሪ መሆን ማለት በጎል መርዳት በማትችልበት ጊዜ በመከላከል ማገዝ ነው። አንተ ጫና በመፍጠር አርአያ ከሆንክ፣ እኛ ምን እንደሚኖረን ታውቃለህ? ድንቅ ቡድን ይኖረናል!”
ምባፔ ከዚያ በኋላ በወቅቱ “ግማሽ ሃሳቡ ማድሪድ ላይ እንደነበር” እና “የሉዊስ ኤንሪኬን ፍልስፍና በሚገባ እንዳልተጠቀመበት” አምኗል። የፈረንሳዩ ካፒቴን አጠቃላዩን የቡድን ፍልስፍና በፍጹም አልተቀበለውም ነበር። መከላከል የማጥቃት ብቃቱን እንደሚያዳክምበት እና በቀድሞ አሰልጣኞቹ የተሰጠውን ነፃነት ለቡድኑ ስኬት ሲል አሳልፎ መስጠት አልፈለገም ነበር።
አሁን የፒኤስጂ የፊት መስመርን የሚመሩት ዴምቤሌ፣ ኽቪቻ ክቫራትስኬሊያ፣ ዴዚሬ ዱዌ እና ብራድሌይ ባርኮላ ግን እንዲህ አይነት ችግር የለባቸውም። በአውሮፓ አምስት ታላላቅ ሊጎች ውስጥ በ90 ደቂቃ ውስጥ ከዱዌ በላይ ከፍተኛ ጫና (press) የፈጠረ ተጫዋች የለም። ክቫራትስኬሊያም በዚህ ረድፍ ውስጥ ከመጀመሪያዎቹ አምስት ውስጥ ይገኛል። ባለፈው የውድድር ዘመን በቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ላይ ዴምቤሌ የያን ሶመርን የግብ መውጫ ኳስ ለመቀማት ሲጠባበቅ የነበረበት ምስል የፒኤስጂ የመጀመሪያው ስኬት ተምሳሌት ነው። መመሪያውን ካልተከተሉ መቀመጫው ተቀያሪ ወንበር ነው፤ ለሶስት ቦታዎች አራት አለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ተጫዋቾች መኖራቸው ደግሞ ዛቻው ተግባራዊ እንደሚሆን ማረጋገጫ ነው።
ነገር ግን ተጫዋቾቹ ራሳቸው፣ በተለይም ዴምቤሌ፣ ደረጃውን ከፍ እያደረጉት ይገኛሉ። “ከምንም በላይ ፒኤስጂ እንዲያሸንፍ መጫወት አለብን፤ ሜዳ ላይ ለብቻችን የምንጫወት ከሆነ ውጤታማ አንሆንም። ባለፈው አመት ከራሳችን በፊት ለክለቡ ቅድሚያ ሰጥተናል፤ ያንን መልሰን ማግኘት አለብን” ሲል በየካቲት ወር ተናግሯል። በቻምፒዮንስ ሊግ የታዩት ብቃቶችም የቡድን አጋሮቹ ሰምተውታል የሚል ፍንጭ ይሰጣሉ። ፒኤስጂ በዚህ የውድድር ዘመን ከአትሌቲኮ ማድሪድ በመቀጠል ኳስ በመንጠቅ (ball recoveries) ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባለፈው አመት በዚህ ረገድ መሪ ነበሩ።
ባለፈው ሳምንት ባየር ሙኒክ ላይ እንዳሳዩት፣ የመከላከል ትጋታቸው ለጨዋታው ውበት፣ ለክህሎት ወይም ለውጤታማነታቸው እንቅፋት አልሆነም። ለዚህም ክቫራትስኬሊያ ማረጋገጫ ነው። ጆርጂያዊው ተጫዋች በቻምፒዮንስ ሊግ 10 ጎሎችን አስቆጥሮ 5 አመቻችቶ አቀብሏል፤ ይህም ለአንድ የፒኤስጂ ተጫዋች በአንድ የውድድር ዘመን ከፍተኛው ክብረ ወሰን ነው። እንዲሁም በስድስት ተከታታይ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ላይ ጎል ያስቆጠረ ወይም አመቻችቶ ያቀበለ አራተኛው ተጫዋች ሆኗል። ዴምቤሌም ባለፈው አመት ተመሳሳይ ውጤት አስመዝግቧል።
በእርግጥ ፒኤስጂ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ረገድ ብቻውን አይደለም። ሊግ 1 ወደ 18 ቡድኖች ዝቅ ማለቱ፣ የኩፕ ዴ ላ ሊግ መቅረቱ እና በፒኤስጂ እና በሌሎች የሀገር ውስጥ ተቀናቃኞቹ መካከል ያለው የፋይናንስ ልዩነት ቡድኑ በዚህ የውድድር ዘመን እንዲህ ያለ ብቃት እንዲያሳይ ረድተውታል። ባየር ሙኒክም በቡንደስሊጋው ተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ስለሚገኝ ተመሳሳይ ብቃት ማሳየቱ አያስደንቅም። ያም ሆኖ የፒኤስጂ ፈጣን እና ከፍተኛ ጫና የመፍጠር ስልት ስኬት አምጥቷል፣ ሌሎች የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦችም ይህንን ለመከተል እየሞከሩ ነው።
ሌሎች ነጥቦች፦
• ፒኤስጂ በመከላከል ውስጥ ደስታን ቢያገኝም፣ ማርሴይ በሀቢብ ቤዬ ስር ሲጫወት ማየት ግን ምንም ደስታ የለውም። ሮቤርቶ ዴ ዜርቢ በየካቲት ወር ከለቀቁ በኋላ የክለቡ ብቃት በእጅጉ ቀንሷል። ጣሊያናዊው አሰልጣኝ ባለፈው አመት “ችግሩ እኔ ከሆንኩ እለቃለሁ” ብለው ነበር። ያለፉት ሳምንታት ግን ችግሩ እሳቸው እንዳልነበሩ አረጋግጠዋል። ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቅዳሜ እለት በናንት 3 ለ 0 መሸነፋቸው ለቻምፒዮንስ ሊግ የማለፍ ተስፋቸውን አጨልሞታል። በውድድር ዘመኑ አምስት ጨዋታዎችን ብቻ ያሸነፈው ናንት በማርሴይ ላይ የደርሶ መልስ ድል በማስመዝገብ የመትረፍ ተስፋውን ሲያለመልም፣ ለቤዬ ግን የመጨረሻው ምስማር ሊሆን ይችላል ተብሏል።
• ፖል ፖግባ ከግንቦት 2023 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሞናኮ በቋሚነት ተሰልፎ ተጫውቷል። ቴክኒካዊ ብቃቱ አሁንም ቢኖርም፣ የፍጥነት መቀነስ ግን ይታይበት ነበር። ሞናኮ ሜትዝን በጭማሪ ሰአት ሲያሸንፍ አንሱ ፋቲ 10ኛው የሊግ 1 ጎሉን አስቆጥሯል። ሜትዝ ላለፉት 13 አመታት ለስምንተኛ ጊዜ ወደ ታችኛው ሊግ ወርዷል። አሰልጣኝ ቤኖይት ታቬኖት በዚህ የውድድር ዘመን በ25 ጨዋታዎች ላይ ድል ባለማግኘታቸው የማይፈለግ ክብረ ወሰን አስመዝግበዋል።
ይህ ዘገባ የጌት ፍሬንች ፉትቦል ኒውስ ነው።