ማንቸስተር ዩናይትድ በደረጃ ሰንጠረዡ በ3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የቅዳሜ ተጋጣሚው ከሆነውና 6ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቼልሲ በሰባት ነጥቦች ይበልጣል። ቡድኑ በስታምፎርድ ብሪጅ በሚኖረው ጨዋታ ይህ ልዩነት እንዲጠበብ አይፈልግም። ከሁለት የውድድር ዘመናት በኋላ ወደ አውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ መመለስ ለዩናይትድ እጅግ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ይህ ደግሞ የተጫዋቾችን ደመወዝ ከፍ ያደርገዋል። በዚህም እስከ 2028 ድረስ ውል ያለው የራሽፎርድ ሳምንታዊ ደመወዝ 325,000 ፓውንድ ይደርሳል። ዩናይትድ ተጫዋቹን ለመሸጥ ፍላጎት ቢኖረውም፣ ይህን ያህል ከፍተኛ ደመወዝ ሊከፍሉ የሚችሉ ክለቦች ጥቂት ናቸው።
“በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የሚሰጥበት ጊዜ ይመጣል፣ ማርከስም በዚህ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል። ነገር ግን እስካሁን የተወሰነ ነገር የለም” ብለዋል ካሪክ። “በእኔ በኩል እዚህ ያለን ማንኛውንም ተጫዋች አብሬው ለመስራት፣ ብቃቱን ለማውጣትና እንዲሻሻል ለመርዳት ዝግጁ ነኝ። በአሁኑ ወቅት ትኩረታችን እዚህ ባለው ስብስብ ላይ ነው፤ በውሰት ላይ ያሉ ተጫዋቾችም አሉ። ወደፊት የሚሆነውን በሂደት እናያለን። እንደ አሰልጣኝ እና እንደ ቡድን መሪ፣ ከእያንዳንዱ ተጫዋች ምርጡን ብቃት ማውጣት እንፈልጋለን።”
ካሪክ ቡድኑ ሰኞ ምሽት በሊድስ ከደረሰበት ሽንፈት እንዲያገግም ቢፈልጉም፣ የተከላካይ መስመር ቀውስ ገጥሟቸዋል። ሃሪ ማጓየር በቦርንማውዙ ጨዋታ በቀይ ካርድ ከወጣ በኋላ ለአራተኛው ዳኛ ባሳየው ባህሪ ተጨማሪ የአንድ ጨዋታ እገዳ ስለተጣለበት በድጋሚ አይሰለፍም። ሊሳንድሮ ማርቲኔዝም በሊድሱ ጨዋታ የዶሚኒክ ካልቨርት-ሌዊንን ፀጉር በመሳቡ በቀይ ካርድ ከሜዳ በመውጣቱ ጨዋታው ያመልጠዋል። ማቲያስ ዴሊግትም ለረጅም ጊዜ በጉዳት ስለሚርቅ ካሪክ በመሃል ተከላካይ እጥረት ተመትተዋል።
ካሪክ ስለ ማጓየር እገዳ ሲናገሩ፦ “ምንም ማድረግ የምንችለው ነገር የለም። በእርግጥ በጣም አዝኛለሁ። ባለፉት ጥቂት ሳምንታት መሰል ሁኔታዎች በማጋጠማቸው በእጅጉ ተበሳጭቻለሁ፣ አሁን ግን ወደፊት መመልከት አለብን” ብለዋል።