League Table

የአርሰናል የጉዳት ዜና፡ የቡካዮ ሳካ ወደ ሜዳ መመለስ አሁንም አጠራጣሪ መሆኑ ተገለጸ

ሚኬል አርቴታ አርሰናል የውድድር ዘመኑን ያለ ዋንጫ ያጠናቅቃል የሚል “ምንም ስጋት” እንደሌለው አረጋገጠ። ሆኖም ቡካዮ ሳካ ከአኪሊስ ተረከዝ ጉዳቱ መቼ ሊያገግም እንደሚችል ከፍተኛ ጥርጣሬ መኖሩን አምኗል። አርሰናል ረቡዕ እለት በሻምፒዮንስ ሊግ ከስፖርቲንግ ጋር ለሚያደርገው የሁለተኛ ዙር ጨዋታ ሲዘጋጅ፣ በሁሉም ውድድሮች ካደረጋቸው ያለፉት አራት ጨዋታዎች በሦስቱ ሽንፈት ገጥሞታል። ይህም ቅዳሜ እለት በፕሪምየር ሊጉ በቦርንማውዝ በገዛ ሜዳው የደረሰበትና ለዋንጫ ተቀናቃኙ ማንቸስተር ሲቲ በር የከፈተውን አስከፊ ሽንፈት ያካትታል።

ባሳለፍነው ሳምንት በፖርቹጋል በተደረገው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ 1-0 ማሸነፉ ለቡድኑ ብቸኛ ስኬት ሲሆን፣ አርቴታ እና ልጆቹ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በተከታታይ ዓመታት በአውሮፓ ታላቅ መድረክ ግማሽ ፍፃሜ የመድረስ ዕድል አላቸው። በቦርንማውዙ ሽንፈት ምክንያት ቡድኑ “ተሸብሯል” የሚል ከፍተኛ ትችት ቢሰነዘርበትም፣ የአርሰናሉ አሰልጣኝ ግን አዎንታዊ አመለካከቱን እንደያዘ ነው። “እንደ እሳት እየነደድኩ ነው። ሌላ ምንም ነገር የለም። ለዚህ ውጤት ለመብቃት ብዙ አልሜያለሁ፤ ምክንያቱም ይህ ክለብ የነበረበትን ሁኔታ አውቃለሁ። አሁን የማየው ውበትንና ዕድልን ብቻ ነው፤ ይህንን ጉዞ ከእኛ ጋር ለተጓዙ ደጋፊዎች ውጤታማ ማድረግ እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ይገባቸዋል፤ ጉዟችንም አስገራሚ ነበር” ብሏል። አክሎም “በየቀኑ የሚያንቀሳቅሰኝም ይሄው ነው። ምንም አይነት ፍርሃት የለኝም። ፍርሃት የነበረኝ ‘ይህንን ካላሳካን ክለቡ ምን ሊሆን ይችላል’ ብዬ አስብ በነበረበት ወቅት ነው። አሁን ግን አላማ፣ እሳት፣ አቅጣጫ እና እንደምናሳካው ሙሉ እምነት ነው ያለኝ” ሲል ተናግሯል።

ሳካ ባለፈው ወር በካራባኦ ካፕ ፍፃሜ በማንቸስተር ሲቲ ከተሸነፉበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ሜዳ አልተመለሰም። አርቴታ ጉዳቱ “ለተወሰነ ጊዜ” አብሮት የቆየ መሆኑን ገልጾ፣ መቼ እንደሚመለስ እርግጠኛ እንዳልሆነ ተናግሯል። “የሳምንታት ሳይሆን የቀናት ጉዳይ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ነገር ግን በልምምድ ወቅት የሚሰጠውን ጫና እንዴት እንደሚቋቋመው ማየት አለብን” ብሏል። አርሰናል ለስፖርቲንጉ ጨዋታ ዩሪየን ቲምበር፣ ሪካርዶ ካላፊዮሪ እና ካፒቴኑ ማርቲን ኦዴጋርድ ላይም ጥርጣሬ አለበት። በተጨማሪም ማክሰኞ እለት ልምምድ ያመለጠው ዲክላን ራይስ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥ አርቴታ ገልጿል። “ብዙ ጨዋታዎችን ተጫውቷል፣ የችግሩ አካልም ይሄው ነው። ነገር ግን ነገ ከእኛ ጋር ለመሆን የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ እርግጠኛ ነኝ” ሲል አሰልጣኙ ተናግሯል።