ቡካዮ ሳካ እና ዩሪየን ቲምበር በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ ቢሆኑም፤ እንደ ጋብሪኤል ማጋልሃኤስ፣ ዲክላን ራይስ እና ሊያንድሮ ትሮሳርድ ያሉ ተጫዋቾች ለፖርቹጋሉ ሻምፒዮን ላይ ለሚደረገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ለአርቴታ መልካም ዜና ሆኗል። የአርሰናሉ አሰልጣኝ ቅዳሜ እለት ከሳውዝሃምፕተን ጋር በነበረው ጨዋታ ጠንካራ ስብስባቸውን ባለማሰለፋቸው ትችት ቢሰነዘርባቸውም፤ ቡድናቸው በውድድሩ ስምንቱን የምድብ ጨዋታዎች በማሸነፍ የመጀመሪያው ቡድን መሆኑን በማስታወስ ነገሮችን በሰፊው እንዲመለከቱ ጠይቀዋል።
“ማድረግ ያለብን ነገር ግልጽ ነው ብዬ አስባለሁ” ያሉት አርቴታ፤ “መደናገጥ ውስጥ ከመግባት ይልቅ ነገሩ ለምን እንደተፈጠረ መረዳት እና ግልጽነትን መፍጠር ያስፈልጋል። ያንን ስንገመግም እና ስንቀበለው ደግሞ የተሻልን እንሆናለን። ማድረግ ያለብንም ይኸው ነው” ብለዋል። አሰልጣኙ ቡድናቸው ጫናዎችን የመቋቋም አቅሙ ያሳስባቸው እንደሆነ ሲጠየቁ፡ “አይደለም። እንደዚህ አይነት እድል ሲኖርህ በደስታ፣ በተሻለ ዝግጅት፣ አሁን ባለህበት ሁኔታ እና ማድረግ ባለብህ ነገሮች ላይ በማተኮር መጠቀም አለብህ። በተለይም ማንነታችንን በተመለከተ፤ እዚህ እንድንደርስ ያደረገን ነገር ግልጽ ነው፣ ትኩረት ማድረግ ያለብንም እዚያ ላይ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
አክለውም “ማንነት የሚገነባው በተግባር እንጂ በቃላት ወይም ማሳካት በምፈልጋቸው ነገሮች አይደለም። እኛ አሁን ላለንበት ደረጃ ያበቁን በርካታ እውነታዎች አሉን” ብለዋል። በተከታታይ ሽንፈቶች ወቅት ኬፓ አሪዛባላጋ ተሰልፎ የነበረ ቢሆንም፤ ከስፖርቲንግ ጋር በሚደረገው ጨዋታ ዴቪድ ራያ ወደ ግብ ጠባቂነት ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል። ራያም “ይህ የእግር ኳስ አካል ነው፤ አንዳንዴ ትመረጣለህ አንዳንዴ ደግሞ አትመረጥም” ካለ በኋላ፤ “ያለፈው አልፏል፤ አሁን ያንን ህመም ለቀሪው የውድድር ዘመን እንደ ነዳጅ ልንጠቀምበት ይገባል” ሲል ተናግሯል።
አርሰናል በአውሮፓ ታላቅ ክለቦች ውድድር ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ በሩብ ፍፃሜው ሲሳተፍ፤ ባለፈው የውድድር ዘመን በዚህ ስታዲየም ስፖርቲንግን 5 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው። በወቅቱ ስፖርቲንግ በጆአኦ ፔሬራ ይመራ የነበረ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት በሩይ ቦርጅስ ስር እጅግ በጥሩ አቋም ላይ ይገኛሉ። ቦርጅስ አርሰናልን ለመግጠም ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ወይ ተብለው ሲጠየቁ፡ “አላምንም። እነሱ ትልቅ ቡድን ናቸው፣ ትልልቅ ቡድኖች ደግሞ ሁልጊዜ ማሸነፍ ይፈልጋሉ። የመጨረሻዎቹን ሁለት ጨዋታዎች መሸነፋቸው ነገሮችን ለእኛ የበለጠ ከባድ ያደርጋቸዋል ብዬ አስባለሁ። እኛ ግን በራሳችን እናምናለን፣ ነገም ስፖርቲንግ ከዚህ ቀደም አድርጎት የማያውቀውን አስደናቂ ነገር እናደርጋለን የሚል እምነት አለን” ብለዋል።