League Table

አርኔ ስሎት አሌክሳንደር ኢሳክ ለፒኤስጂው የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ዝግጁ እንደሚሆን አረጋገጡ

የሊቨርፑሉ ዋና አሰልጣኝ አርኔ ስሎት አሌክሳንደር ኢሳክ ከደረሰበት የእግር ስብራት ጉዳት እያገገመ መሆኑን እና ከፓሪስ ሴንት ዠርሜን ጋር ለሚደረገው የሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ዝግጁ እንደሚሆን አረጋግጠዋል። በ125 ሚሊዮን ፓውንድ የብሪታንያ የዝውውር ክብረወሰንን በመስበር ሊቨርፑልን የተቀላቀለው ስዊድናዊው አጥቂ፣ ካለፈው ታህሳስ 11 ጀምሮ ወደ ሜዳ ያልገባ ሲሆን እስካሁን ሙሉ ልምምድ ባይጀምርም፣ ሚያዝያ 8 በፓርክ ደ ፕሪንስ ለሚደረገው ጨዋታ ግን እንደሚደርስ ታውቋል። ይህም የአውሮፓ ሻምፒዮኑን ፒኤስጂ ለማሸነፍ ለሚጥሩት ሊቨርፑሎች ትልቅ መነቃቃትን ይፈጥራል።

ኢሳክ ለአራት ወራት ያህል ከሜዳ ርቆ በመቆየቱ በቋሚነት ለመጀመር ዝግጁ ባይሆንም፣ ለስሎት ግን ከተቀያሪ ወንበር ጥሩ አማራጭ እንደሚሆን ይጠበቃል። ቅዳሜ ከብራይተን ጋር ለሚደረገው ጨዋታ ሞሃመድ ሳላህን እና አሊሰንን በጡንቻ ጉዳት ምክንያት እንደማያገኝ የገለፀው ስሎት፣ “ኢሳክ ለጨዋታው ይደርሳል” ብሏል። አሰልጣኙ አክለውም “ጥያቄው ምን ያህል ዝግጁ ነው የሚለው ነው። ከአንድ አመት በፊት በካራባኦ ካፕ ፍፃሜ ላይ የገጠመንን እና በእለቱ እጅግ ድንቅ የነበረውን ተጫዋች የምትጠብቁ ከሆነ፣ ለወራት ከቆየ በኋላ በዛ ብቃት ላይ ይገኛል የሚል ጥርጣሬ አለኝ። ነገር ግን ለተወሰኑ ደቂቃዎች ልጠቀምበት እንደምችል እገምታለሁ” ብለዋል።

ኢሳክ እስካሁን ከዋናው ቡድን ጋር አንድም ቀን ልምምድ አለመስራቱን የገለፁት ስሎት፣ “ከአንድ ልምምድ በኋላ 45 ወይም 90 ደቂቃ መጫወት አይቻልም። አሁን ላይ የልምምድ ጨዋታ ማዘጋጀት ብንፈልግ እንኳ ፌዴሪኮ ቺዬሳ፣ ከርቲስ ጆንስ እና ጆ ጎሜዝ ብቻ ስለሆኑ ያሉን ሶስት ለሶስት ነው የምንጫወተው፤ ሌላው የቡድኑ አባል ከጋላታሳራዩ ጨዋታ በኋላ በማገገም ላይ ነው። አሌክስ ለብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎችም ገና ዝግጁ አይደለም፤ ዝግጁ ቢሆን ኖሮ ከስዊድን ብሄራዊ ቡድን ጋር ይሆን ነበር” ሲሉ አስረድተዋል።

ኢሳክ በክረምቱ ከኒውካስል ወደ አንፊልድ ለማምራት ባደረገው ጥረት የቅድመ ውድድር ዝግጅት ስላመለጠው ብቃቱን ለማግኘት ወራትን ወስዶበት ነበር። ቢሆንም ስሎት የ26 አመቱ አጥቂ በውድድር አመቱ መገባደጃ ላይ ተፅዕኖ መፍጠር እንደሚችል ያምናሉ። “እሱን መልሰን ለማግኘት እንደ ደጋፊዎቹ እኔም ጓጉቻለሁ። ምክንያቱም በ90 በመቶ ጨዋታዎቻችን ከተጋጣሚ የተሻለ የግብ እድል እንፈጥራለን። ከዓለም ምርጥ አጥቂዎች አንዱ በቡድናችን ውስጥ ቢኖር ኖሮ ከዚህ የተሻለ ነጥብ ይኖረን ነበር” ብለዋል። አሰልጣኙ አክለውም ኢሳክ ሙሉ ብቃቱን የሚያሳየው በሚቀጥለው የውድድር አመት እንጂ በማንቸስተር ሲቲ ወይም በፒኤስጂ ጨዋታ ላይ እንዳልሆነ ጠቁመዋል። “ለማንቸስተር ሲቲ ጨዋታ ይደርሳል ብዬ አላስብም፣ ነገር ግን በሚቀጥሉት ሁለት ወራት እንደምንጠቀምበት እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል።

ሞሃመድ ሳላህ ረቡዕ እለት ከጋላታሳራይ ጋር በነበረው ጨዋታ በደረሰበት የጡንቻ ጉዳት ለጥቂት ሳምንታት ከሜዳ እንደሚርቅ ታውቋል። ስሎት ተጫዋቹ መቼ እንደሚመለስ ግልፅ ጊዜ ባይሰጥም፣ የብራይተኑን ጨዋታ ጨምሮ ግብፅ ከሳውዲ አረቢያ እና ስፔን ጋር የምታደርጋቸውን የወዳጅነት ጨዋታዎች እንደሚያመልጡት ተረጋግጧል። አሊሰን ቤከርም ወደ ብራይተን ያልተጓዘ ሲሆን በእሱ ምትክ ጊዮርጊ ማማርዳሽቪሊ ይሰለፋል። አሊሰን ከብራዚል ብሄራዊ ቡድንም ስሙን ሰርዟል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሊቨርፑል በኢብራሂማ ኮናቴ ላይ የተሰነዘረውን “አፀያፊ እና ዘረኝነት የተሞላበት ስድብ” አጥብቆ አውግዟል። ኮናቴ ከጋላታሳራዩ ጨዋታ በኋላ በማህበራዊ ሚዲያ ዘረኛ ስድቦች የደረሱበት ሲሆን፣ ክለቡ የማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች እንዲህ አይነት የጥላቻ ንግግሮች እንዳይሰራጩ መከላከል ባለመቻላቸው ወቅሷል። ኮናቴ በጨዋታው ወቅት የጋላታሳራዩ አጥቂ ቪክቶር ኦሲምሄን እጅ እንዲሰበር ምክንያት በሆነው አጋጣሚ ውስጥ በመሳተፉ፣ በማህበራዊ ሚዲያ አባቱ መሞታቸውን ጨምሮ በዲዮጎ ጆታ ላይም ስድቦች ተሰንዝረዋል።

ክለቡ ባወጣው መግለጫ “ይህ ድርጊት ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው፣ የሰው ልጅን ክብር የሚያዋርድ እና በጥላቻ ላይ የተመሰረተ ነው” ብሏል። “ተጫዋቾቻችን የጥቃት ኢላማ አይደሉም፤ እነሱ የሰው ልጆች ናቸው። በማህበራዊ ሚዲያ በስም ባልታወቁ አካውንቶች የሚሰነዘሩት ጥቃቶች ለስፖርቱ እና ለሚፈቅዱት ተቋማት ትልቅ እድፍ ነው። ኩባንያዎቹ ኃላፊነት ወስደው አሁኑኑ እርምጃ መውሰድ አለባቸው። ዘረኝነት እንዲስፋፋ መፍቀድ ምርጫ ነው፤ ይህ ደግሞ ተጫዋቾችን እና ቤተሰቦቻቸውን መጉዳቱን ቀጥሏል። ይህ ሁኔታ ሊቀጥል አይገባም፤ ነገ ሳይሆን ዛሬውኑ ሊቆም ይገባል” ሲል ክለቡ አሳስቧል።