እሁድ በፕሪሚየር ሊግ ከሰንደርላንድ ጋር የሚጋጠሙት ኤዲ ሀው፣ “ራሴን ለማነቃቃት ምንም ችግር የለብኝም፣ ይልቁንም ለተጫዋቾቹ ነው የሚያሳስበኝ” ብለዋል። አክለውም “እኔ ከጨዋታዎች እና ከግምገማ ሂደቶች በፍጥነት የመውጣት ችሎታ አለኝ። አሁን ትኩረታችን በሙሉ በሰንደርላንድ ላይ ነው። ስለ ዛሬው ሳይሆን ለአንድ ትልቅ ጨዋታ በአእምሮም በአካልም ዝግጁ መሆናችንን ማረጋገጥ ነው ዋናው ነገር። ይህ ጨዋታ ለኛ ጥሩ አጋጣሚ ይመስለኛል” ሲሉ ተናግረዋል።
“የእሁዱ ጨዋታ እጅግ ትልቅ ነው። አሁን ስለ እሱ ማውራት ይከብደኛል። ልክ ለህይወታችን እንደምንዋጋ አድርገን መጫወት አለብን። ይህ ለከተማዋ፣ ለደጋፊዎች፣ ለተጫዋቾች እና ለጠቅላላው ክለብ ትልቅ ጨዋታ ነው። ይህንን ሽንፈት በፍጥነት ተቋቁመን ወደ እሁዱ ጨዋታ ማተኮር አለብን” በማለት ሀው አሳስበዋል። ሀው ቡድናቸው በካምፕ ኑ በመጀመሪያው 45 ደቂቃ ባሳየው እንቅስቃሴ እና ሁለት ግቦችን በማስቆጠሩ አዎንታዊ ጎኖች እንደነበሩ ቢገልጹም፣ በመጀመሪያው አጋማሽ መጨረሻ ላይ የተቆጠረባቸው ግብ ያስከተለውን ስነ-ልቦናዊ ጫና መቋቋም አለመቻላቸውን እና በመከላከል ረገድ የተሰሩ ስህተቶች በመሪነት ወደ እረፍት እንዳይወጡ ማድረጋቸውን አምነዋል።
“በሴንት ጀምስ ፓርክ ለ90 ደቂቃ፣ ዛሬ ደግሞ ለግማሽ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር አድርገናል። የውጤቱ መጥፎ መሆን ያንን ሁሉ ሊያስረሳ አይገባም። ውጤቱ ጨዋታው እንዴት እንደነበረ አይገልጽም” ብለዋል ሀው። “የመከላከል ብቃታችን ከቼልሲ ጋር እንደነበረው አልነበረም። በመጀመሪያው ግብ ላይ ሁለት ተጫዋቾች ተንሸራተዋል። ከዚያም የቆመ ኳስ ስህተት ነበር። ትልቁ ቅጽበት ደግሞ የፍጹም ቅጣት ምቱ ነው። በመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ በጣም ጥሩ ብንጫወትም እና መሆን የምንፈልገውን ቡድን ብናንጸባርቅም፣ ብዙ ስህተቶችን ሰርተናል።”
“መከላከል በሚገባን መንገድ ብንከላከል ኖሮ፣ በመጀመሪያው አጋማሽ መሪ ሆነን እንወጣ ነበር። ከዚያም ሌላ በቆመ ኳስ ግብ ተቆጠረብን። የመጀመሪያዎቹ አራት ግቦች ከእኛ የማይጠበቁ ነበሩ፤ እንደዛ ግብ ሊቆጠርብን አይገባም ነበር። ሁለቱ በቆመ ኳስ የተቆጠሩ ግቦች ተራ ስህተቶች በመሆናቸው ይቅር የማይባሉ ናቸው። እንደዛ ሊሆን አይገባም ነበር። ከላሚን ያማል የፍጹም ቅጣት ምት በኋላ በአእምሮ ደረጃ ያገገምን አይመስለኝም” ሲሉ ሀው ጨምረው ገልጸዋል።