በአሜክስ ስታዲየም የነበረው ምሽት በስሜት የተሞላ ነበር። የብራይተኑ አሰልጣኝ ፋቢያን ሁርዝለር ከጨዋታው በፊት አርሰናል ጊዜ ያባክናል ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበው የነበረ ሲሆን፣ በጨዋታው ወቅትም ሆነ ከጨዋታው በኋላ ዳኞች ጊዜ የማባከን ስልትን መቆጣጠር ባለመቻላቸው አርሰናል ተጠቃሚ ሆኗል በሚል ተቆጥተዋል።
አርሰናል ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ከተጋጣሚዎቹ የተለያዩ ትችቶች እየተሰነዘሩበት ይገኛል። ወልቭስ ከቡድኑ ጋር 2 ለ 2 ከተለያየ በኋላ በቲክቶክ ገጹ የአርሰናልን የጨዋታ አያያዝ የሚተች ተንቀሳቃሽ ምስል አጋርቷል። በተጨማሪም ክለቡ በቆሙ ኳሶች ላይ ስላለው ጥንካሬና ስለሚከተለው ስልት የሞራልና የውበት ጥያቄ የሚያነሱ በርካታ ቅሬታዎች እየተሰሙ ነው።
ሳካ ግን እንዲህ ይላል፦ “ለእነዚህ ነገሮች ጆሮ አንሰጥም። አላየውም፣ አላነበውምም። በምንም መልኩ ጠቃሚ አይደለም። እኛ በራሳችን መንገድ ማሸነፋችንን መቀጠል እንፈልጋለን። ሰዎች የፈለጉትን ይላሉ። እጅግ ማራኪ እግር ኳስ ብንጫወትም ሆነ በቆመ ኳስ ግብ ብናስቆጥር ወሬያቸው አይቀርም። ለእኛ ዋናው ጨዋታዎችን ማሸነፍ ነው፣ የወቅቱም ማብቂያ እየተቃረበ ነው።”
በኦፕታ መረጃ መሰረት፣ አርሰናል በብራይተኑ ጨዋታ ኳስን ዳግም ለማስጀመር የወሰደበት አጠቃላይ ጊዜ 30 ደቂቃ ከ 51 ሰከንድ ሲሆን፣ ይህም በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከፍተኛው ነው። የብራይተን ደግሞ 16 ደቂቃ ከ 07 ሰከንድ ነበር። አርሰናል ኳስን ዳግም ለማስጀመር በአማካይ 31.4 ሰከንድ የወሰደ ሲሆን፣ ይህም በሊጉ 12ኛው ከፍተኛው ነው። ኳስ በጨዋታ ላይ የነበረችበት መቶኛ 53.5% ሆኖ ተመዝግቧል።
የሳካ የግል አሀዛዊ መረጃዎችም ሲፈተሹ ከባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት አንጻር ግቦቹና ለግብ የሆኑ ኳሶች (assists) ቀንሰዋል። በብራይተን ላይ ያስቆጠራት ግብ በሊጉ ስድስተኛው፣ በሁሉም ውድድሮች ደግሞ ዘጠነኛው ነው። በሊጉ አምስት፣ በአጠቃላይ ደግሞ ሰባት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቷል።
“እንደ አጥቂ አንዳንዴ በአሀዛዊ መረጃዎች ላይ የበለጠ አስተዋጽኦ ማድረግ ትፈልጋለህ፣ ግን በተመሳሳይ ማሸነፍም ትፈልጋለህ” ብሏል ሳካ። “ሁለቱንም ማመጣጠን ያስፈልጋል። በዚህ መልኩ እንቀጥል፤ በዚህ ደረጃ ላይ ሆነን ካጠናቀቅን እኔ ደስተኛ ነኝ።”
ሳካ የጨዋታው ፍጻሜ ሲሰማና ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው ከኖቲንግሃም ፎረስት ጋር 2 ለ 2 መለያየቱ ሲነገረው ትልቅ ደስታ እንደተሰማው ገልጿል። “ደጋፊዎቻችንን ለማመስገን ስንሄድ በጩኸት ሲያስተጋቡ በሌላው ጨዋታ የሆነ ነገር መፈጠሩን ተረዳሁ። ከዚያም ሚኬል አርቴታ መጥቶ ሲቲ አቻ መውጣቱን ነገረኝ” ብሏል። “በእርግጥም ጥሩ ግስጋሴ ላይ ነን። በተከታታይ ሶስት ትልልቅ ጨዋታዎችን በስፐርስ፣ በቼልሲ እና በብራይተን ላይ አሸንፈናል። በራስ መተማመን ተሰምቶናል፣ ተነሳስተናልም።”