ደ ዜርቢ ለቡድኑ ደካማ አጀማመር በርካታ ምክንያቶችን የጠቀሱ ሲሆን፣ ዋናው ምክንያት በኒውዚላንድ እና አውስትራሊያ በተደረገው የረጅም ርቀት የቅድመ-ውድድር ዝግጅት ጉዞ ወቅት በርካታ ተጫዋቾች ላይ የደረሰው ጉዳት መሆኑን ገልጸዋል። የአለም ዋንጫ የተጫዋቾችን የመመለሻ ጊዜ በማዘግየቱ ስላሳደረው ተፅዕኖ የገለጹት አሰልጣኙ፣ ሳቪዮ እና ኦማር ማርሙሽ የዝውውር መስኮቱ ሊዘጋ ሲል ዘግይተው ቡድኑን መቀላቀላቸውንም እንደ ሌላ ምክንያት ጠቅሰዋል።
አሰልጣኙ በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ተጫዋቾቻቸው ያሳዩትን ጥሩ እንቅስቃሴ ቢያደንቁም፣ በኋላ ግን ጉልበት እንደጠፋቸውና የስነ-ልቦና ችግር እንደታየባቸው አምነዋል። “በጣሊያንኛ ‘ስብሎካርሲ’ (sbloccarsi) የሚል ቃል አለ፤ ትርጉሙም ራስን መክፈት ወይም ነፃ ማውጣት ማለት ነው” ያሉት ደ ዜርቢ፣ “አራት ጨዋታዎች ያለ ድል እና ያለ ጎል ማለፉ ለተጫዋቾቹ ከባድ በመሆኑ የስነ-ልቦና መዘጋት (mental block) ውስጥ ናቸው። ቡድኑ በጣም ጠንካራ ነው፣ ጎል ማስቆጠርና ጨዋታዎችን ማሸነፍ እንችላለን። የተጫዋቾቹን ታሪክ ማክበር አለብን፤ ዶሚኒክ ሶላንኬን እና ማርሙሽን ትተን ሌሎቹን ብንመለከት በታሪካቸው ብዙ ጎሎችን ያስቆጠሩ አይደሉም፣ ስለዚህ እነዚህን ጎሎች ለማግኘት መጣር አለብን። በጨዋታ ጥራታችን ይህን ማድረግ እንደምንችል አምናለሁ” ብለዋል።
ደ ዜርቢ ወደ ቅድመ-ውድድር ዝግጅት ጉዞው በመመለስ የተለመደ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። “በተለያዩ ምክንያቶች ዘንድሮ ዘግይተን ነው የጀመርነው፤ በጣም ዘግይተናል። ብዙ ተጫዋቾች በዓለም ዋንጫ ላይ ነበሩ፣ ብዙ ጉዳቶች እና በአውስትራሊያም ብዙ ችግሮች ነበሩ። ሚኪ ቫን ደ ቬን፣ ዶሚ ሶላንኬ እና ጄምስ ማዲሰን በአውስትራሊያ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ማቲውስ ፈርናንዴዝም እዚያው ተጎድቶ ለ15 ቀናት ያህል ልምምድ አምልጦታል፣ ይህም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ሳቪዮ እና ማርሙሽ ደግሞ ከመጡ ገና 10 ቀናቸው ነው። ከሙሉ ቡድኑ ጋር መስራት የጀመርኩት ከሁለት ሳምንት በፊት ባለው ሀሙስ እንጂ ባለፈው ሀሙስ አይደለም። ስለዚህ ገና ትክክለኛው የአካል ብቃት ደረጃ ላይ አልደረስንም” ሲሉ አስረድተዋል።
“በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች በጣም ጥሩ ተጫውተናል፤ ነገር ግን ምናልባት ጉልበት በማለቁ ወይም ጎል ባለማስቆጠራችን የተወሰኑ ተጫዋቾች በራስ የመተማመን መንፈሳቸው ቀንሶ ሊሆን ይችላል። አዎንታዊ ብቻ ሳይሆን እውነታውን መጋፈጥ አለብን። ያን የጨዋታ ብቃታችንን ወደ 60፣ 70 ወይም 90 ደቂቃዎች ማሳደግ ከቻልን ብዙ ጨዋታዎችን እንደምናሸንፍ እርግጠኛ ነኝ። በሜዳው የመጨረሻ ሶስተኛ ክፍል (last third) ላይ መሻሻል እንዳለብን ግልጽ ነው። የመጨረሻው ውሳኔ፣ የመጨረሻው ኳስ እና በተለይ ቦታና ጊዜ ስናገኝ ብዙ ሙከራዎችን ማድረግ አለብን። ሆኖም ስለ ተጫዋቾቼ ምንም መጥፎ ነገር መናገር አልችልም” ሲሉ ደ ዜርቢ ንግግራቸውን አጠቃለዋል።