አርኔ ስሎትን የተኩት አዲሱ አሰልጣኝ አንዶኒ ኢራኦላ በዚህ የክረምት የዝውውር መስኮት ለክንፍ ተጫዋቾች ቅድሚያ ሰጥተው እየሰሩ ይገኛሉ። የቀድሞው የበርንማውዝ አሰልጣኝ የክለቡን የፊት መስመር መልሶ ለመገንባት በሚያደርጉት ጥረት ባርኮላ ከቪክቶር ሙኞዝ በመቀጠል ወደ ቡድኑ የተቀላቀለ ተጫዋች ሆኗል።
ባርኮላ በሰጠው አስተያየት “ዝውውሩ ረጅም ጊዜ ወስዷል፣ ነገር ግን ዛሬ ለሊቨርፑል መጫወት በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። አሁን የምፈልገው ሜዳ ገብቼ መጫወት ብቻ ነው” ብሏል። አክሎም “ትልቅ ስኬት እንደማገኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ከሁሉም በላይ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማሸነፍ በህይወቴ ካሉኝ ትልልቅ ህልሞች አንዱ ነው። ይህንን ለማሳካት እና በቡድኑ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ለመቆየት ነው ረጅም ኮንትራት የፈረምኩት” ሲል ህልሙን ገልጿል።
የፊታችን ረቡዕ 24ኛ ዓመት ልደቱን የሚያከብረው ባርኮላ፣ ሊቨርፑል ለበርካታ የውድድር ዓመታት ሲከታተለው የቆየው ተጫዋች ነው። የቀድሞው የሊዮን ተጫዋች ከሌሎች ክለቦች ጥያቄ ቢቀርብለትም ወደ ሊቨርፑል ለመምጣት ብቻ ቆርጦ በመነሳቱ ዝውውሩ እስኪጠናቀቅ ፒኤስጂ ተተኪ ተጫዋቾችን እስኪያገኝ ድረስ መጠበቅ ግድ ሆኖ ነበር። ባርኮላ ሲቀጥልም “ሊቨርፑል እንደሚፈልገኝ ባወቅኩ ጊዜ ምንም አላመነታሁም፤ ለኔ በጣም ትልቅ ክለብ እንደሆነ አውቅ ነበር” ብሏል።
ፈረንሳዊው ተጫዋች የሊቨርፑል የመጨረሻው ፈራሚ ሊሆን ቢችልም፣ ኮዲ ጋክፖ ወደ ማንቸስተር ሲቲ የሚያመራ ከሆነ ግን ሁኔታው ሊቀየር ይችላል። ሊቨርፑል ሆላንዳዊውን ተጫዋች ለመሸጥ የሚያስበው ለክለቡ የሚጠቅም ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው። ሊቨርፑል በዚህ የዝውውር መስኮት የ21 ዓመቱን ጄረሚ ዣኬት እና የ23 ዓመቱን ሙኞዝን በማስፈረም ለረጅም ጊዜ የሚያገለግል በወጣት ተጫዋቾች የተገነባ ቡድን ለመፍጠር እያለመ መሆኑን አሳይቷል።