የሲቲን የማሬስካ ፍላጎት ሊያወሳስበው የሚችለው ጉዳይ አሰልጣኙ አሁንም ከቼልሲ ጋር የውል ግዴታዎች እንዳለባቸው መታመኑ ነው። ማሬስካ ከቼልሲ ሲለቁ በውላቸው ላይ ሶስት አመት ከግማሽ እንዲሁም የክለቡ ተጨማሪ የአንድ አመት ምርጫ እንደነበረ ይነገራል። ዘ አትሌቲክ እንደዘገበው ከሆነ ደግሞ፣ ማሬስካ ከቼልሲ ከመልቀቃቸው ሳምንታት በፊት ከሲቲ ሰዎች ጋር ስለ ጋርዲዮላ ተተኪነት ሁለት ጊዜ ተነጋግረው እንደነበር ለቼልሲ አሳውቀዋል። ማሬስካ በጥር ወር ቼልሲ ከሲቲ ጋር ሊጫወት ጥቂት ቀናት ሲቀሩት በድንገት መልቀቁ የእግር ኳሱን አለም አስደንግጦ ነበር።
ጋርዲዮላ ውላቸውን እስከመጨረሻው ለማክበር ሊወስኑ ቢችሉም፣ በኢትሃድ ስታዲየም ትልቅ ለውጥ እንደሚመጣ የእግር ኳስ ሰዎች በስፋት እየተነጋገሩበት ይገኛል። ይህም ሲቲ አማራጭ እቅዶችን እንዲያወጣ አስገድዶታል። ሂደቱን በበላይነት እየመሩት ያሉት የእግር ኳስ ዳይሬክተሩ ሁጎ ቪያና ሲሆኑ፣ አዲስ አሰልጣኝ ካስፈለገ ማሬስካ የጋርዲዮላ ተተኪ የመሆን እድላቸው ከፍተኛ ነው። ጋርዲዮላ ባለፈው ታህሳስ ወር ማሬስካን “በአለም ላይ ካሉ ምርጥ አሰልጣኞች አንዱ” ሲሉ የገለጿቸው ሲሆን፣ በቼልሲ የነበራቸው ቆይታም ልዩ እንደነበር ተናግረዋል።
ሁለቱ አሰልጣኞች በሲቲ አብረው ከሰሩ በኋላ የጠበቀ ግንኙነት አላቸው። ሲቲ በ2023 ሻምፒዮንስ ሊግን ሲያሸንፍ ማሬስካ የጋርዲዮላ ረዳት ነበሩ፤ እንዲሁም የጋርዲዮላን የአጨዋወት ዘይቤ ይከተላሉ። ሲቲ አርሰናልን በመብለጥ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እየተፋለመ ሲሆን፣ ሌላ የሀገር ውስጥ የሶስትዮሽ ድል ሊያሳካ ይችላል። ጋርዲዮላ በእንግሊዝ እግር ኳስ ሁሉንም ነገር ያሳኩ በመሆናቸው፣ በኢትሃድ ለ10 አመታት ከቆዩ በኋላ እረፍት ቢወስዱ የሚደነቅ አይሆንም። በሲቲ 18 ዋንጫዎችን ያነሱ ሲሆን፣ አምስት ጨዋታዎች እየቀሩም በጎል ልዩነት ሊጉን እየመሩ ነው።
ጋርዲዮላን የሚተካ ማንኛውም አሰልጣኝ፣ በ2013 ሰር አሌክስ ፈርጉሰንን የተኩት ዴቪድ ሞይስ የገጠማቸውን አይነት ከባድ ፈተና እንደሚጠብቀው ይታመናል። ማሬስካ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው አሰልጣኝ ሲሆኑ፣ ወደ ጋርዲዮላ ረዳትነት ከማደጋቸው በፊት የሲቲ ከ23 አመት በታች ቡድን አሰልጣኝ ነበሩ። በ2024 ሌስተር ሲቲን ወደ ፕሪሚየር ሊግ ካሳደጉ በኋላ ማውሪሲዮ ፖቼቲኖን በመተካት ቼልሲን ተቀላቅለዋል። በመጀመሪያው አመት ቡድኑን ለሻምፒዮንስ ሊግ ማብቃት የቻሉ ሲሆን፣ የኮንፈረንስ ሊግ እና የክለቦች የአለም ዋንጫን ማሸነፍ ችለዋል። ሆኖም ሁለተኛው የውድድር ዘመናቸው ባልተጠበቀ ሁኔታ ተቋርጧል።
በርካታ የቼልሲ ተጫዋቾች በማሬስካ አሰልጣኝነት ይደሰቱ የነበረ ሲሆን፣ በመልቀቃቸውም አዝነዋል። ኤንዞ ፈርናንዴዝ እና ማርክ ኩኩሬላ ባለፉት ሳምንታት ስለ ቀድሞ አሰልጣኛቸው መልካም ምስክርነት ሰጥተዋል። ሲቲ አማካይ ክፍሉን ለማጠናከር በሚያደርገው ጥረት ከኤንዞ ፈርናንዴዝ ጋር ስሙ እየተያያዘ ይገኛል። ቼልሲ አርጀንቲናዊውን ለመሸጥ ፈቃደኛ ቢሆንም ከፍተኛ ዋጋ እንደሚጠይቅ ይጠበቃል። ማንቸስተር ሲቲ ስለ ጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጥ ተጠይቆ ምላሽ አልሰጠም።