League Table

“የፕሪሚየር ሊጉ ውሳኔ በሚገርም ሁኔታ ርኅራኄ የታየበት ነው”፦ ቼልሲ ከቅጣት አምልጧል?

ቼልሲ በሮማን አብራሞቪች የስምንት ዓመታት የስኬት ዘመን የእግር ኳስ ደንቦችን በመጣሱ የፕሪሚየር ሊጉ ቦርድ የሰጠው ፍርድ ክለቡ “በማታለል እና በመደበቅ” ተግባር ላይ መሰማራቱን አረጋግጧል። ከ30 በላይ የሚሆኑት እነዚህ ጥሰቶች እንደ ኤደን ሀዛርድ፣ ዊሊያን፣ ዴቪድ ልዊዝ እና ኔማንጃ ማቲች ያሉ ታዋቂ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ከተደረጉ የዝውውር ውሎች ጋር በተያያዘ በሂሳብ መዝገብ ላይ ያልሰፈሩ ቢያንስ 47 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያዎችን ይመለከታሉ። በአብራሞቪች የባህር ማዶ ኩባንያዎች መረብ በኩል የተከናወኑት እነዚህ ሚስጥራዊ ግብይቶች እ.ኤ.አ. በ2023 በጋርዲያን እና በዓለም አቀፍ አጋሮቹ በተደረገ የምርመራ ዘገባ ይፋ መሆናቸው ይታወሳል።

የጥሰቶቹ ክብደት ከፍተኛ ቢመስልም የተጣለው ቅጣት ግን በአንጻራዊ ሁኔታ ቀላል የሆነ 10.75 ሚሊዮን ፓውንድ የገንዘብ ቅጣት እና ተግባራዊ ላይሆን የሚችል የዝውውር እገዳ ነው። ታዲያ ቼልሲ በቀላል ቅጣት አምልጧል? ወደፊትስ ከበድ ያሉ ቅጣቶች ይጠብቁት ይሆን? ይህ ቅጣት ቼልሲን ይጎዳዋል ወይ ከተባለ መልሱ “አይደለም” የሚል ነው። ክለቡን ከአብራሞቪች የገዛው የክሊርሌክ ኮንሰርቲየም በ2.5 ቢሊዮን ፓውንድ የሽያጭ ውል ውስጥ 150 ሚሊዮን ፓውንድ “ተቀናሽ” እንዲሆን የሚያደርግ አንቀጽ አስገብቷል። ይህ ገንዘብ በአብራሞቪች ዘመን ለተፈጸሙ ድርጊቶች የሚመጡ ወጪዎችን ለመሸፈን ለአምስት ዓመታት ተይዞ የሚቆይ ነው።

ዩኤፋ (Uefa) እ.ኤ.አ. በ2023 በአብራሞቪች ዘመን ያልተሟላ የፋይናንስ ሪፖርት በማቅረቡ ቼልሲን ከ8.5 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ቀጥቶት ነበር። አሁን የፕሪሚየር ሊጉን ቅጣት ጨምሮ አጠቃላይ ድምሩ ቼልሲ እ.ኤ.አ. በ2019 ኤደን ሀዛርድን ለሪያል ማድሪድ በመሸጥ ካገኘው ገቢ አንድ አራተኛውን እንኳን አይሞላም። ከዚህም በላይ በቀጣይ ለሚመጡ ማናቸውም ቅጣቶች የሚሆን በቂ ገንዘብ በተያዘው ፈንድ ውስጥ ይገኛል። የታገደው የዝውውር እገዳም ቢሆን ተግባራዊ የሚሆነው ቼልሲ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ተጨማሪ ጥሰቶችን ከፈጸመ ብቻ ነው። ስለዚህ ክለቡ ያለምንም ችግር ሁለቱንም ቅጣቶች ተቋቁሞ ጉዞውን መቀጠል ይችላል።

ይህ የቅጣት ተፅዕኖ ማነስ ጥሰቶቹ በተፈጸሙባቸው ዓመታት (ከ2011-2018) ቼልሲ ካገኛቸው ጥቅሞች ጋር መታየት ይኖርበታል፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ክለቡ ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን፣ ሻምፒዮንስ ሊግን፣ ሁለት የኤፍኤ ካፕ ዋንጫዎችን እና አንድ የሊግ ካፕ ማሸነፍ ችሏል። ክለቡ ከዚያ በኋላም ቢሆን በአብራሞቪች ዘመን በተጣለው የስኬት መሰረት ላይ በመቆም በርካታ ዋንጫዎችን አንስቷል። ታዲያ ይህ የምሕረት ውሳኔ ነው? በማካርቲ ዴኒንግ የሕግ ተቋም የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ እና የእግር ኳስ ፋይናንስ ባለሙያ የሆኑት ስቴፋን ቦርሰን “የፕሪሚየር ሊጉ ቦርድ አቀራረብ በሚገርም ሁኔታ ርኅራኄ የታየበት ነው” ብለዋል።

ባለሙያው ፕሪሚየር ሊጉ በቅርቡ በሌስተር ሲቲ፣ ኖቲንግሃም ፎረስት እና ኤቨርተን ላይ በፈጸሙት የትርፋማነት እና ዘላቂነት ደንብ ጥሰት ምክንያት የነጥብ ቅነሳ ቅጣቶችን ለመጣል የነበረውን ጉጉት ጠቅሰዋል። ቦርሰን እንዳሉት ፕሪሚየር ሊጉ ቼልሲ ከፈጸማቸው ጥሰቶች “ስፖርታዊ ብልጫ” ማግኘቱን አለመጥቀሱ እንደ ነጥብ ቅነሳ ያሉ ስፖርታዊ ቅጣቶች ያልተላለፉበት ምክንያት ሊሆን ይችላል። “ቼልሲ እንደ ዊሊያን እና ሀዛርድ ያሉ ተጫዋቾችን ለማስፈረም በፉክክር ውስጥ በነበረበት ወቅት 47 ሚሊዮን ፓውንድ ከሂሳብ መዝገብ ውጭ መክፈሉን አምኗል፤ ይህም በጽሑፍ በሰፈረው የቅጣት ስምምነት መሠረት ሆን ተብሎ የተደረገ እና ማታለልን ያካተተ ነው። እነዚህ ነገሮች በቀጥታ ከስፖርታዊ ስኬት ጋር የተያያዙ ከባድ ጉዳዮች ናቸው። እንዲህ ያሉ አስከፊ ድርጊቶች በተለመደው አሠራር ስፖርታዊ ቅጣትን ያስከትሉ ነበር” ብለዋል።

ነገር ግን ቼልሲ ጥፋቱን በራሱ ጊዜ አምኖ አልገለጸም? ክለቡ ምሕረት የተደረገለት አዲሶቹ ባለቤቶች አንዳንድ ጥሰቶችን በራሳቸው ጊዜ ሪፖርት በማድረጋቸው ነው። ነገር ግን የፍርድ ውሳኔው እንደሚያረጋግጠው ምርመራው “ክለቡ ራሱ ይፋ ካደረጋቸው ጉዳዮች በላይ ሰፊ” እና ሌሎች በርካታ የምርመራ እርምጃዎችን ያካተተ ነበር። ቦርሰን ጥሰቱን በራስ ተነሳሽነት ማሳወቅ ፋይዳ ሊኖረው ይገባል ወይ የሚለውን ይጠይቃሉ፤ በተለይም የአሁኑ ክለብ ካለፈው ድርጊት የተነሳ እያገኘ ያለውን ጥቅም ግምት ውስጥ በማስገባት። “አንድን ንግድ ስለሸጡ ብቻ ካለፈው ታሪክ ጋር ያለው ግንኙነት ይቋረጣል ማለት አይደለም። ማንቸስተር ሲቲ ነገ ክለቡን ቢሸጥ ማንም ሰው በእሱ ላይ የቀረቡት የደንብ ጥሰት ክሶች ይሰረዛሉ ብሎ አይጠብቅም” ብለዋል።

የእንግሊዝ እግር ኳስ ማኅበር (FA) አሁንም የነጥብ ቅነሳ ሊያደርግ ይችላል? አዎ። ማኅበሩ ባለፈው ዓመት በቼልሲ ላይ 74 የደንብ ጥሰት ክሶችን የመሰረተ ሲሆን ምርመራው አሁንም ቀጥሏል። ምንም እንኳን የውሳኔው ውጤት ባይታወቅም፣ የዛሬው የፕሪሚየር ሊግ ብይን ላይ የተቀመጠው ቋንቋ ትኩረት የሚስብ ነው። ብይኑ እንደሚለው የሊጉ ቦርድ “በኤፍኤ ክሶች ምክንያት በክለቡ ላይ ሊጣል የሚችለውን ቅጣት” ከግምት ውስጥ አስገብቷል። ይህ ምናልባት ፕሪሚየር ሊጉ ኤፍኤም የዩኤፋን እና የእሱን አርአያ በመከተል በገንዘብ ቅጣት ብቻ ይወሰናል ብሎ ማመኑን ሊያሳይ ይችላል። ወይም ደግሞ ኤፍኤ ስፖርታዊ ቅጣት ይጥላል ብሎ ስለሚጠብቅ ፕሪሚየር ሊጉ ራሱ ስፖርታዊ ቅጣት መጣል አስፈላጊ ሆኖ አላገኘውም ማለት ሊሆን ይችላል።

ቀጣዩ እርምጃ ምንድነው? የቼልሲ ባለቤቶች በማንኛውም ጊዜ ሊወጣ የሚችለውን የኤፍኤ ውሳኔ እስኪሰሙ ድረስ ሙሉ በሙሉ ሊረጋጉ አይችሉም። ክለቡ እና ፕሪሚየር ሊጉም በቅጣት በተሸፈነው ጊዜ ውስጥ ስለተከናወኑ ድርጊቶች ተጨማሪ ጥያቄዎችን ሊያስነሱ የሚችሉ አዳዲስ መረጃዎች እንዳይወጡ ተስፋ ያደርጋሉ። እንደዛ ዓይነት ነገር ቢከሰት ለሁሉም አካላት አሳፋሪ ሊሆን ይችላል። ለጊዜው ግን ቦርሰን ቼልሲ እፎይታ ያገኘ ይመስላቸዋል። “የቼልሲ ጠበቆች በጣም ጥሩ ሥራ ሰርተዋል። በቀድሞ ባለቤቶች ዋስትና ተሰጥቷቸዋል፤ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ከባድ ቅጣቶችን ለመጣል የሚገፋፋውን ፕሪሚየር ሊግን ማሳመን ችለዋል” ብለዋል። አክለውም የቼልሲ የደንብ ጥሰት ተፅዕኖ በተግባር የሚያርፈው በዩክሬን ጦርነት ተጎጂዎች ላይ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ የሆነበት ምክንያት የገንዘብ ቅጣቱ የሚከፈለው ከክለቡ ሽያጭ ገቢ ላይ ተቀንሶ ከተያዘው ገንዘብ በመሆኑ ነው። አብራሞቪች ያንን ገንዘብ በጦርነቱ ለተጎዱ ሰዎች ለመለገስ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም፣ ይህ ዕቅድ በኦሊጋርኩ እና በብሪታንያ መንግሥት መካከል ባለ አለመግባባት ምክንያት እስካሁን አልተፈታም።