League Table

የጥበብ እና የባህል ማማ፦ የአውሮፓ መገናኛ ብዙኃን በፒኤስጂ እና ባየር ሙኒክ አስደናቂ ጨዋታ ተደመሙ

የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን ፓሪስ ሴንት ዠርሜን በሻምፒዮንስ ሊግ 100ኛ ድሉን ያስመዘገበበትንና በክለቡ ታሪክ “ከምርጦቹ አንዱ” ተብሎ የተወደሰውን ውጤት በደስታ ተቀብለውታል። ባየር ሙኒክ በሚቀጥለው ረቡዕ በሜዳው በሚያደርገው የግማሽ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታ በፓሪስ የታየውን የግብ ናዳ ለመድገም ተስፋ ያደርጋል። ማክሰኞ ዕለት በፓሪስ የተመዘገበው የ5 ለ 4 ውጤት በውድድሩ የግማሽ ፍፃሜ ታሪክ ከፍተኛው የግብ መጠን ሆኖ ተመዝግቧል። ‘ሌኪፕ’ (L’Équipe) ጨዋታውን “አስገራሚ ጥንካሬ እና ቴክኒካዊ ብቃት የታየበት ታላቅ ጦርነት” ሲል ገልጾታል፤ በተለይም እያንዳንዳቸው ሁለት ግቦችን ያስቆጠሩትን የክቪቻ ኳራትስኬሊያ እና ኡስማን ዴምቤሌን ብቃት አድንቋል። የእግር ኳስ ተንታኙ ቪንሰንት ዱሉክ ጨዋታውን “የስሜት እና የፍላጎት ማዕበል” ሲል የጠራው ሲሆን “የዘመናዊ እግር ኳስን ምርጥ ገጽታ ያሳየ” መሆኑንም ገልጿል።

‘ለ ፓሪዚያን’ (Le Parisien) በበኩሉ ጨዋታውን “ፍጹም እብደት፣ የጥበብ እና የባህል ማማ፣ የአለም ድንቆች ሙዚየም እና ለታሪክ መጽሐፍት የሚሆን አፈ ታሪክ” ሲል አወድሶታል። ሆኖም ባየር ሙኒክ በጨዋታው መገባደጃ ላይ ያሳየው መነሳሳት በመልሱ ጨዋታ ሊረዳው እንደሚችል በማሳሰብ፦ “ሁለቱም ወገኖች ወደ ኋላ ለማፈግፈግ አይፈልጉም፤ ውጤቱም በሁለቱም ቡድኖች እጅግ ጠንካራ በሆኑት የማጥቃት መስመሮች ጉልበት ላይ የተመሰረተ ይሆናል” ሲል አስጠንቅቋል።

በጀርመን በኩል ጋዜጦች በባየር ሙኒክ የመከላከል ድክመት ላይ ትኩረት ቢያደርጉም፣ ክለቡ ከ 5 ለ 2 መሪነት ተነስተው በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ልዩነቱን ማጥባታቸው ለመልሱ ጨዋታ ተስፋ እንዲሰንቁ አድርጓቸዋል። ‘ኪከር’ (Kicker) ጨዋታውን በፓርክ ዴ ፕሪንስ የታየ “የእግር ኳስ ፌስቲቫል” እና “አስደናቂ ፍልሚያ” ሲል ጠርቶታል። ባየር ሙኒክ በዳዮት ኡፓሜካኖ እና በሉዊስ ዲያዝ ግቦች ወደ 5 ለ 4 በመመለስ “የማይበገር ማንነት” ማሳየቱን ዘግቧል። ‘ሱዳይቸ ዘይቱንግ’ (Süddeutsche Zeitung) የባየር ሙኒኩ አሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ በቅጣት ምክንያት ከሜዳ ውጭ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ አሰልጣኙ ከመልሱ ጨዋታ በፊት “እምነታችን 100 በመቶ ነው” ማለታቸውን አስፍሯል። ‘ቢልድ’ (Bild) በበኩሉ ውጤቱን “ዱርዬ እና ግልጽ የእግር ኳስ ጦርነት” ሲል ገልጾታል።

የጣሊያን መገናኛ ብዙኃን በኳራትስኬሊያ ብቃት ተደንቀዋል። ‘ላ ጋዜታ ዴሎ ስፖርት’ (La Gazzetta dello Sport) “ኳራ” ውጤቱን 1 ለ 1 ለማድረግ ያስቆጠራትን ግብ “የጥበብ አስማት” ሲል አሞካሽቷል። ጨዋታውንም “ፍጹም እይታ፤ እውነተኛ እና ንጹህ እግር ኳስ” ሲል ገልጾታል። ‘ኮሪየር ዴሎ ስፖርት’ (Corriere dello Sport) በበኩሉ ጨዋታውን “የእግር ኳስ ከፍተኛው ጥግ” ቢለውም፣ የባየርን አጨዋወት ግን “አንዳንዶች በስሜት የተሞላ እና ፈጣን ሲሉት፣ ሌሎች ደግሞ በፕሌይ ስቴሽን (PlayStation) ላይ ብቻ የሚታይ ጨዋታ ነው” በማለት የአስተያየት ልዩነቶችን አንጸባርቋል።

ስፔን ውስጥ ትኩረቱ ከባርሴሎና ጋር ግንኙነት ባላቸው ሉዊስ ኤንሪኬ እና ዴምቤሌ ላይ ነበር። ኤንሪኬ “እስካሁን ካሰለጠንኳቸው ጨዋታዎች ምርጡ ነው” ሲሉ፣ ‘ማርካ’ (Marca) ደግሞ ጨዋታውን “ለመጨረሻው ጨዋታ ከሚደረግ ፍልሚያ ይልቅ የማጥቃት ብቃት የታየበት ትርኢት ይመስል ነበር” ሲል አድንቋል። ‘ኤ ኤስ’ (AS) በበኩሉ “የማያቋርጥ ድራማ” የታየበት መሆኑን ገልጾ የባየርን የማሸነፍ ስነ-ልቦና እና ለመልሱ ጨዋታ ያላቸውን ምኞት አድንቋል።