League Table

“የድል ሽታ አግኝተናል”፤ ኦሬይሊ የዌምብሌይ ድል ለማንቸስተር ሲቲ የሊግ ግስጋሴ አዲስ ጉልበት እንደሚሰጥ ተናገረ

ኒኮ ኦሬይሊ ማንቸስተር ሲቲ እሁድ እለት በካራባኦ ካፕ ፍፃሜ አርሰናልን 2-0 ካሸነፈ በኋላ የአርሰናልን የዘጠኝ ነጥብ መሪነት ለማጥበብ “የድል ሽታ አግኝተናል” ሲል ገለጸ። በዌምብሌይ ስታዲየም ኦሬይሊ በሁለተኛው አጋማሽ በግንባር በመግጨት ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች የሚኬል አርቴታን ቡድን በማሸነፍ ለሲቲ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ትልቅ ዋንጫ አስገኝተዋል።

የፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን ከመሪዎቹ ክለብ አንድ ቀሪ ጨዋታ ያላቸው ሲሆን በሚቀጥለው ወር ደግሞ በኢቲሃድ ስታዲየም ያስተናግዷቸዋል። በሲቢኤስ ስፖርት ጎላዞ (CBS Sports Golazo) ላይ የ21 ዓመቱ ተጫዋች አርሰናልን ስለማሳደድ ተጠይቆ ሲመልስ፦ “አዎ 100%። የድል ሽታው ሁሌም ነበር፤ በራሳችን እንተማመናለን፤ እንደምንችለውም እናውቃለን። ወደ እኛ ሜዳ መምጣት አለባቸው፣ ይህም በዚህ የውድድር ዘመን ሁሉም እንዳየው ከባድ እንደሚሆንባቸው ግልጽ ነው። ስለዚህ የድል ሽታው አፍንጫችን ላይ ነው፣ ወደፊት መቀጠል አለብን” ብሏል።

“ይህ የዋንጫ ድል ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥርልናል፣ አሁን ግስጋሴያችንን መቀጠል ነው ያለብን። በእርግጥ ለእነሱ (ለአርሰናል) ትልቅ ድንጋጤ ነው። ልክ እኛ ከሪያል ማድሪድ ጋር ከመጫወታችን በፊት እንደነበረው ሁሉ እነሱም ለሁሉም ዋንጫዎች ይፋለሙ ነበር” ሲል አክሏል። ኦሬይሊ ከሪያል ማድሪድ ጋር በነበረው ጨዋታ ከግራ ተከላካይነት ወደ አማካይ ክፍል መቀየር ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል አልሸሸገም። “ከባድ ሊሆን ይችላል፣ በበርናባው ከሪያል ማድሪድ ጋር በነበረው ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ላይ እንደታየው ትንሽ የምቸገርባቸው ጨዋታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ከጀርባዬ ክፍተቶች ተፈጥረው ነበር፣ ስለዚህ ቦታ መቀያየር ከባድ ቢሆንም እኔ ለመሆን የምመኘው አይነት አለም አቀፍ ደረጃ ያለው ተጫዋች ለመሆን ግን ከተለያዩ ቦታዎች ጋር መላመድ መቻል አለብህ” ሲል ገልጿል።

ሲቲ ለአርሰናል የግብ እድሎችን እንዴት እንደፈጠረ ሲገልጽ፦ “ከራያን ቸርኪ ጋር በመሆን በቀኝ በኩል ያለውን ክፍተት መጠቀም ነበር። ዲክላን ራይስ ወደ ሮድሪ ወይም በርናርዶ ሲልቫ ለመጠጋት ስለሚሞክር ቸርኪ ነፃ እንደሚሆን አይተናል፣ ግቦቹም የተገኙት ከዚያው ከቀኝ በኩል ነው” ብሏል። የኦሬይሊ የቡድን አጋር ሮድሪም የዌምብሌይ ድል በሊጉ ፉክክር ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል ብሎ ያምናል። ሮድሪ ሲናገር፦ “በጣም ትልቅ ተጽዕኖ አለው። ለዚህ ነው ይህ ጨዋታ ለዚህ ዋንጫ ብቻ ሳይሆን እነሱን ማሸነፍ እንደምንችል ለማሳየት ጭምር ነው የምለው። ገና ብዙ የሚቀሩ ስራዎች አሉ፣ ከሻምፒዮንስ ሊግ መውጣት ባንፈልግም አሁን ግን ትኩረታችንን ለጨዋታዎች ዝግጅት በምናገኘው ሰፊ ጊዜ ላይ ማድረግ አለብን።”

“የሪያል ማድሪድ ጨዋታ በጣም ከባድ ነበር ነገር ግን ቡድኑ አገግሟል። ከአርሰናል ጋር የነበረው ጨዋታ ለዋንጫው ብቻ ሳይሆን በሊጉ ምርጥ ከሚባለው ቡድን ጋር የምንፋለምበት በመሆኑ በጣም አስፈላጊ እንደነበር እናውቃለን። አሁን ማረፍ እና ለቀሪዎቹ ሁለት ውድድሮች በከፍተኛ ተስፋ መመለስ አለብን።” ሲቲ በሚቀጥለው የኤፍኤ ካፕ ሩብ ፍፃሜ ሊቨርፑልን የሚገጥም ሲሆን የ29 ዓመቱ ሮድሪ የደጋፊዎችን ድጋፍ አድንቋል። “ደጋፊዎቻችን ሁሌም ከጎናችን ናቸው፣ በተሳካላቸውም ሆነ በከፉ ጊዜያት አልተለዩንም” ብሏል።

በዌምብሌይ አርሰናል ሲቲን ከራሳቸው ግብ ክልል እንዳይወጣ ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉም በመጀመሪያው አጋማሽ መጨረሻ ላይ ሲቲ ብልጫ መውሰድ ጀምሮ ነበር። ጋርዲዮላ በእረፍት ሰዓት ምን እንዳላቸው ሲጠየቅ፦ “የተረጋጋ ንግግር ነበር – ነገሮችን በጥሩ ሁኔታ እያከናወንን እንደነበር ነገረን። ጫና በመፍጠር በኩል ጥሩ ነበርን፣ ዋናው ነገር ጨዋታውን ለመቆጣጠር በራስ መተማመን ማሳየት ነበር። በአካላዊ ብቃት በኩል ትንሽ እንደቀነሱ ተረድተን ነበር፣ እኛም ያንን ተጠቅመን ሄድንባቸው። እንደ ኒኮ ኦሬይሊ ያሉ በግብ ክልል ውስጥ ጎበዝ የሆኑ ተጫዋቾች ሲኖሩህ ልዩነት መፍጠር ይቻላል” ሲል ሮድሪ ንግግሩን አጠቃሏል።