ብሩኖ ፈርናንዴዝ በአጥቂ አማካይነት የጨዋታው ቀማሪ ሲሆን፣ ማቲየስ ኩኛ፣ ምቤውሞ እና ራሽፎርድ በግል ክህሎታቸውና በታክቲክ ነፃነታቸው የተጋጣሚን ተከላካይ ክፍል ለማተራመስ ይሞክራሉ። ነገር ግን ይህ ቀመር ገና ፍጹም አልሆነም። ይህ እንዲሰራም እያንዳንዱ ተጫዋች የራሱንና የሌሎችን ሚና ጠንቅቆ ማወቅ ይኖርበታል። በፕሪሚየር ሊጉ ፍጥነት ላይ ማንኛውም መዘግየት ወይም ጥርጣሬ የአጥቂ መስመሩን እንቅስቃሴ ገና ሳይጀመር ሊያበላሸው ይችላል። ተጫዋቾቹ ሜዳ ላይ አብረው ብዙ ጊዜ ካላሳለፉ በስተቀር በዋጋቸው ብቻ ውጤታማ መሆን አይችሉም።
የቡድኑ አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ኩኛን እንደ ‘ፎልስ 9’ (false 9) በመጠቀም ተጫዋቹ በፈለገበት ቦታ እየተንቀሳቀሰ የተጋጣሚን ተከላካይ እንዲያጠቃ ነፃነት ሰጥቶታል። ኩኛ በዎልቭስ በነበረበት ወቅት ከርቀት ኳሶችን በመምታት ይታወቅ ነበር። አሁን ግን በዩናይትድ ፈርናንዴዝ በሚገኝበት ቦታ ላይ ስለሚንቀሳቀስ የራሱን ዘይቤ ለመቀየር ተገድዷል። በሌላ በኩል ምቤውሞ ከመስመር ወደ ውስጥ መግባት ሲመርጥ፣ ራሽፎርድ ግን ተከላካዮችን በማለፍ በኩል የተሻለ ነው። ራሽፎርድ ጊዜያዊውን ተከላካይ መርሊን ሮልን አጣብቂኝ ውስጥ ቢከተውም፣ ይህ ድርጊት ግን ብዙም ሲደገም አልታየም።
ዩናይትድ ኳስን ተቆጣጥሮ ኤቨርተንን ወደ ኋላ ቢያፈገፍግም፣ ግብ ጠባቂው ጆርዳን ፒክፎርድ ለረጅም ጊዜ ሳይፈተን ቆይቷል። ፈርናንዴዝም ቢሆን የቡድን አጋሮቹን በሚፈልገው ቦታ ሊያገኛቸው አልቻለም። የተሳሳቱ ኳሶችና ወደ ሜዳ ውጭ የሚወጡ ቅብብሎች የጨዋታው መለያ ነበሩ። በስምንተኛው ደቂቃ ራሽፎርድ፣ ምቤውሞ እና ፈርናንዴዝ ተቀናጅተው የፈጠሩት ሙከራ በግቡ አግዳሚ ቢመለስም፣ በአጥቂ መስመሩ በኩል የታየው ብርታት ግን አነስተኛ ነበር።
ምቤውሞ በ47ኛው ደቂቃ ግብ ቢያስቆጥርም፣ ቡድኑ የሚጠበቅበትን ያህል የበላይነት ሊያሳይ አልቻለም። ቤንጃሚን ሴስኮ ተቀይሮ እስኪገባ ድረስ በኩኛ ይመራ የነበረው የፊት መስመር ግልጽ የሆነ የትኩረት ነጥብ አልነበረውም። ሴስኮ ያስቆጠረው ግብ ከፈርናንዴዝ የተላከለትን ኳስ ሉክ ሾው አመቻችቶለት በጭንቅላቱ በመግጨት ነበር። ይህ እንቅስቃሴ ሁሉም ተጫዋቾች የየራሳቸውን ሚና በሚገባ የተረዱበትና በቀላል መንገድ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ያሳየ ነበር። ፈርናንዴዝ ሉክ ሾው ወደ ፊት እንደሚሮጥ ሲረዳ፣ ሾው ደግሞ ሴስኮ የት ቦታ እንደሚጠብቀው ማሰብ እንኳን አላስፈለገውም።
በሁለተኛው አጋማሽ የታየው ለውጥ የዩናይትድ ስብስብ የተለያዩ አማራጮች እንዳሉት አሳይቷል። እንደ ፓትሪክ ዶርጉ እና ሴስኮ ያሉ ተጫዋቾች ቀጥተኛ የሆነ አጨዋወት ይዘው መግባት ችለዋል። ፈርናንዴዝ፣ ምቤውሞ፣ ራሽፎርድ እና ኩኛ ከፍተኛ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች ቢሆኑም፣ የግል ብቃት ሁልጊዜም የተቀናጀ ቡድን ለመፍጠር ዋስትና አይሆንም። ተጫዋቾቹ በሳምንት ሁለት ጊዜ መጫወታቸው መግባባታቸውን ሊያሳድገው ይችላል። ይህ ካልሆነ ግን ካሪክ ወደ ቀላሉና ብዙም ዘመናዊ ወዳለሆነው ‘ፕላን ቢ’ ለመመለስ ሊገደድ ይችላል።