League Table

ዣቪ ሲመንስ በደረሰበት ከባድ ጉዳት ቀሪውን የውድድር ዘመንና የአለም ዋንጫውን ያመልጠዋል

የቶተንሃሙ አማካይ ዣቪ ሲመንስ የጉልበት ጅማት (ACL) በመበጠሱ ለስምንት ወራት ያህል ከሜዳ እንደሚርቅ ታውቋል። ተጫዋቹ ጉዳቱ የደረሰበት ቅዳሜ ዕለት ቡድኑ በዎልቭስ ላይ 1-0 ድል ባስመዘገበበት ጨዋታ ላይ ሲሆን፣ በቀሪው የፕሪሚየር ሊግ የህልውና ትግል ላይ ለክለቡ ግልጋሎት አይሰጥም። ይህም ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ ክረምት በዓለም ዋንጫ ለኔዘርላንድ ብሔራዊ ቡድን የመሰለፍ ተስፋው መክኗል።

ሲመንስ በሞሊኒው ስታዲየም በ63ኛው ደቂቃ ላይ ኳስን ተከታትሎ ለማውጣት በሚሞክርበት ወቅት ጉልበቱ ተጠምዝዞ በቃሬዛ ለመውጣት ተገዷል። ይህ ለተጫዋቹም ሆነ ለክለቡ ትልቅ መርዶ ሲሆን፣ አዲሱ አሰልጣኝ ሮቤርቶ ዴ ዜርቢ ከሊጉ ላለመውረድ በሚያደርጉት ትግል የ23 ዓመቱን ተጫዋች የፈጠራ ችሎታ በእጅጉ ይፈልጉት ነበር።

ስፐርስ በዎልቭስ ላይ ድል ቢቀናቸውም፣ ይህም በ16 የሊግ ጨዋታዎች የመጀመሪያቸው ቢሆንም፣ አሁንም በደረጃ ሰንጠረዡ 18ኛ ላይ ይገኛሉ። አራት ጨዋታዎች እየቀሩ ከ17ኛው ዌስትሃም በሁለት ነጥቦች ዝቅ ብለው ይገኛሉ። ዴ ዜርቢ በዎልቭሱ ጨዋታ በጉዳት ዘጠኝ ተጫዋቾችን ያላገኙ ሲሆን፣ አጥቂው ዶሚኒክ ሶላንኬም በጡንቻ ጉዳት በጨዋታው ወቅት ተቀይሮ ወጥቷል። ስፐርስ ቀጣይ ጨዋታቸውን እሁድ ከአስቶን ቪላ ጋር ያደርጋሉ።

ሲመንስ በኢንስታግራም ገጹ ባስተላለፈው ልብ የሚነካ መልዕክት “ሕይወት ጨካኝ ልትሆን ትችላለች ይላሉ፣ ዛሬም ያንን እየተሰማኝ ነው” ብሏል። “የእኔ የውድድር ዘመን በድንገት አክትሟል፤ ይህንንም ለመቀበል እየሞከርኩ ነው። በሐቀኝነት ልቤ ተሰብሯል። አንዳቸውም ትርጉም አይሰጡኝም። የፈለኩት ለቡድኔ መታገል ብቻ ነበር፤ አሁን ግን ያ ዕድልና የዓለም ዋንጫው ተነጥቀውብኛል” ሲል ስሜቱን ገልጿል።