ስሎት 16 ሽንፈቶችን ባስተናገደበት አስከፊ የውድድር ዘመን ምክንያት ከፍተኛ ጫና ውስጥ ይገኛሉ፤ ይህ ቁጥር ተቀባይነት እንደሌለውም እራሳቸው ያውቃሉ። ሆኖም ዋና አሰልጣኙ እሳቸው እና የስፖርት ዳይሬክተሩ ሪቻርድ ሂዩዝ እንዲሁም የፌንዌይ ስፖርትስ ግሩፕ (FSG) ባለቤቶችን ጨምሮ የክለቡ አመራሮች፣ ከክሎፕ በኋላ ሊመጣ ስለሚችለው የግዴታ የሽግግር ወቅት እና ለችግሮቹ መንስኤዎች ላይ ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው አረጋግጠዋል። ከሽግግር ጋር ተያይዞ የሚመጣው ውጥረት በባለፈው የውድድር ዘመን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ምክንያት መዘግየቱን ስሎት ያምናሉ።
ታላቁን የሊቨርፑል ቡድን ስለመበተን ሲናገሩ ስሎት፦ “ይህ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ጀምሮ የተስማማንበት ጉዳይ ነው” ብለዋል። “በእግር ኳስ ውስጥ እንዲህ አይነት ዑደቶች መኖራቸው የተለመደ ነው። ሞ (ሳላህ) እና ሮቦ (ሮበርትሰን) ባለፈው ክረምት ካስፈረምናቸው ተጫዋቾች ጋር አብረው በመስራታቸው ደስተኛ ነኝ፤ ምክንያቱም አዲሶቹ ተጫዋቾች ክለቡ ለእነሱ ምን ማለት እንደሆነ እና ምን ያህል ጠንክረው እንደሚሰሩ እንዲያዩ አድርገዋል። በስኬታማ ክለቦች ወይም በማንኛውም ክለብ ውስጥ የአንድ ዑደት ማብቂያ መኖሩ የተለመደ ሂደት ነው። ይህ ለእኛ አዲስ ነገር አይደለም። ትልቁ ነገር ምናልባት በባለፈው የውድድር ዘመን ያንን ዑደት እንዲራዘም ማድረጋችን ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ስሎት አሁንም ቢሆን የሂዩዝ፣ የኤፍኤስጂ የእግር ኳስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ማይክል ኤድዋርድስ፣ የባለቤቶቹ እና ምንም እንኳን ተከታታይ ሽንፈቶች ቢኖሩም “ሊገርም ቢችልም” የሊቨርፑል ደጋፊዎች ድጋፍ እንዳላቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። አሰልጣኙ ሲቀጥሉም፦ “ሁልጊዜ ‘እንደግፍሃለን፣ እንደግፍሃለን’ እያሉ መናገራቸው አይደለም። ነገር ግን እየሆነ ያለውን ነገር እንነጋገራለን፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ‘እየደገፍኩህ ነው’ ብሎ መናገር አያስፈልግም፣ ድጋፉ ይሰማሃል። እዚህ ከመጣሁ ጀምሮ ያ ድጋፍ ተሰምቶኛል። እርስ በእርሳችን ምን እንደምንነጋገር ልነግራችሁ አልችልም፤ ነገር ግን ሰዎች ምን እንደሚጽፉ ባላውቅም እኛ ሁላችንም የምናየው ተመሳሳይ ነገር ይመስለኛል። ይህም ሲባል ባለቤቶቹ፣ ሪቻርድ፣ ማይክል እና ሁሉም ማለት ነው። ሁሉም ሰው በፊታችን ምን እየሆነ እንዳለ እያየ ነው፤ በምናየው ነገር እና ለዛም በሆኑት ምክንያቶች ላይ ሁላችንም አንድ አይነት አቋም አለን” ብለዋል።