ስሎት ሳላህ ኮንትራቱ ሊጠናቀቅ 12 ወራት እየቀረው ለመልቀቅ የወሰነበትን ምክንያት ለራሱ ለተጫዋቹ መተው እንዳለበት ያምናሉ። ሳላህ በታኅሣሥ ወር በሊድስ ዩናይትድ ጨዋታ ወቅት በሰነዘረው ግልጽ ትችት ምክንያት ስሎት በተወሰኑ ወገኖች ዘንድ ለሳላህ መልቀቅ እንደ “መጥፎ ሰው” ተደርገው እንደሚታዩ ተገልጾላቸዋል። አሰልጣኙ በዚህ የውድድር ዓመት ካጋጠሙ ቅር የሚያሰኙ ውጤቶች በኋላ በሊቨርፑል ደጋፊዎች ዘንድ ስላላቸው ተቀባይነት ሲናገሩ “በአሁኑ ወቅት ያለው አጠቃላይ ሁኔታ እንደዛው ነው አይደል?” ብለዋል።
ሆኖም ስሎት ከክለቡ ታዋቂ ተጫዋች ጋር የነበረውን ሁኔታ ከዚህ በተለየ መንገድ እንደማይይዙት አጥብቀው ተናግረዋል። “አዎ [በያዝኩበት መንገድ ደስተኛ ነኝ]” ሲሉ ያስረዱት ስሎት፤ “ወደዚህ የውድድር ዓመት መለስ ብዬ ስመለከት ከዚህ የተሻሉ ሊሆኑ የሚችሉ ውሳኔዎችን ማሳለፍ እንደምችል አስባለሁ፣ ነገር ግን ይህን የምለው በተለይ ከሞ (ሳላህ) ጋር ስላለው ጉዳይ አይደለም። አብረን በቆየንባቸው አንድ ዓመት ተኩል ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ጊዜያት ውስጥ ባደረኳቸው አብዛኞቹ ነገሮች አልፀፀትም” ብለዋል። “ተጫዋቹ ካልተሰለፈ መልቀቅ ይፈልጋል የሚለው ግምት – እውነታው እንደዛ ቢሆን ኖሮ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ይለቅ ነበር። እኔ እዚህ ከመምጣቴ በፊት [በሚያዝያ 2024 በየርገን ክሎፕ ስር] በዌስትሃም የሜዳ ውጪ ጨዋታ ሳይሰለፍ የቀረበትን ጊዜ አስታውሳለሁ። በወቅቱ ለመልቀቅ አልወሰነም ነበር” ሲሉ አክለዋል።
“በነዚህ ጨዋታዎች ካልተሰለፍክ በድንገት መልቀቅ ትፈልጋለህ የሚለው ግምት ብቻ ነው። ግምቱ እውነት ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፣ ነገር ግን ታሪክ እንደሚያሳየው ቀደም ሲል እንዲህ አላደረገም፣ ከዚያ በኋላም ድንቅ የውድድር ዓመት አሳልፏል” ብለዋል። ሳላህ በታኅሣሥ ወር ውስጥ በስድስት ቀናት ውስጥ በሦስት ጨዋታዎች ላይ በተጠባባቂ ወንበር ላይ እንዲቀመጥ መደረጉን ተከትሎ ክለቡ ለሊቨርፑል መጥፎ ውጤቶች ተጠያቂ እያደረገው እንደሆነና ከስሎት ጋር ያለው ግንኙነትም የለም የሚል ክስ አቅርቦ ነበር። ነገር ግን አሰልጣኙ ያ አለመግባባት የ33 ዓመቱ ተጫዋች በአንፊልድ ያለውን አስደናቂ የስፖርት ዘመን እንዲያበቃ ምክንያት ሆኗል ብለው አያምኑም።
“ስለ ጉዳዩ መናገር የሚችለው ብቸኛው ሰው ሞ ራሱ ነው” ያሉት ስሎት፤ “ለስድስት ቀናት ከጨዋታ ውጪ ስለነበረ መልቀቅ ይፈልጋል የሚል ግምት እየወሰዳችሁ ነው። የምትሉት ነገር እውነት ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም። ሞ ለምን ይህን ውሳኔ እንደወሰነ ሃሳቡን የሚያጋራበት ጊዜ ባይኖር ይገርመኛል። ያንን ማድረግ የእኔ ድርሻ አይደለም፣ የእሱ ፋንታ ነው። በእነዚህ ሁሉ ግምቶች ውስጥ መግባት አልፈልግም፤ በግምቶች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል” ብለዋል።
የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ሳላህ በዚህ ክረምት በነጻ ዝውውር እንዲለቅ መፈቀዱ ክለቡ ተጫዋቹን በመሸኘቱ ደስተኛ እንደሆነ ያሳያል የሚለውንም አስተያየት አስተባብለዋል። ቅዳሜ ዕለት ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ለሚደረገው የኤፍኤ ካፕ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ አሌክሳንደር ኢሳክን በተጠባባቂ ወንበር ላይ ሊይዙ የሚችሉት ስሎት “እነዚህ የእናንተ ቃላት ናቸው” ብለዋል። “ሞ መቼ መልቀቅ እንዳለበት የመወሰን ሙሉ መብት እንዳለው አምናለሁ። ለዚህ ክለብ ብዙ ነገሮችን አድርጓል። የራሱን ውሳኔ መወሰን አለበት፣ ያደረገውም ያንኑ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። የሲቲው ጨዋታ ለሊቨርፑልና ለስሎት ወሳኝ ምዕራፍ መጀመሪያ ቢሆንም፣ በስራቸው ላይ ጫና ቢኖርም የ47 ዓመቱ አሰልጣኝ ለዘንድሮው የክረምት የዝውውር መስኮት በሚደረገው እቅድ ላይ በንቃት እየተሳተፉ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። “አዎ እየተሳተፍኩ ነው፣ ይህን ጥያቄ ለምን እንደጠየቃችሁኝም አውቃለሁ” ሲሉ ንግግራቸውን አጠቃለዋል።