አርሰናል አድካሚ በሆነው የውድድር ዘመን በአራት ግንባሮች ሲፋለም ቆይቷል። ቅዳሜ ከፉልሃም ጋር ለሚያደርጉት እና የዋንጫ ተስፋቸውን ለማለምለም ለሚፈልጉበት ጨዋታ ቀደም ብሎ በርካታ የጉዳት ችግሮች አጋጥመዋቸዋል። ፒኤስጂ እና ባየርን በየሊጎቻቸው ያላቸው የበላይነት ማክሰኞ ዕለት በፓሪስ በነበረው አስደሳች ጨዋታ ወቅት በጥሩ አቋም ላይ እንዲገኙ እንዳደረጋቸው አርቴታ ጠቁሟል።
“የባየርን እና የፒኤስጂ ጨዋታን ስመለከት፣ የሁለቱ ቡድኖች ጥራት እና በተለይም ተጫዋቾቹ ያሳዩት የግል ብቃት ምናልባትም ካየኋቸው ጨዋታዎች ሁሉ ምርጡ ሊሆን ይችላል፤ እንዲህ ያለ ነገር አይቼ አላውቅም” ብሏል አርቴታ። “ነገር ግን የተጫዋቾቹን የጨዋታ ደቂቃ እና ትኩስነት ስመለከት አልተገረምኩም። ያን ያህል ጥራት ያለው ጨዋታ ለማሳየት በጣም ትኩስ መሆን አለብህ፤ በሊጎቹ መካከል ያለው ልዩነት እና የፉክክር መንገዱ እንደ ሰማይና ምድር ይራራቃል። በቅርቡ የወጡ ስታቲስቲክሶችን ማየት ብቻ በቂ ነው። እያነፃፀርን ያለነው ሁለት የተለያዩ ዓለማትን ነው። አንዱን ክፍል ያለ አውዱ ማነፃፀር ፍትሃዊ አይመስለኝም” ሲል አክሏል።
አርሰናል ፉልሃምን ካሸነፈ ከሲቲ በስድስት ነጥብ ይርቃል፤ ምንም እንኳን የፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች ቢኖሩትም። የፉልሃም ጨዋታ በአርሰናል እና በአትሌቲኮ ማድሪድ መካከል ካለው የሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ መሃል የተሰገሰገ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል። ማርቲን ኦዴጋርድ በጉልበት ጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ሊርቅ እንደሚችል ስጋት ያለ ሲሆን፣ ይህም የካይ ሀቨርትዝ እና የዩሪየን ቲምበርን አለመኖር የበለጠ ከባድ ያደርገዋል።
ካለፉት የዋንጫ ፉክክር ልምዶች ምን እንደተማረ የተጠየቀው አርቴታ፡ “ሁሉንም ተጫዋቾች በብቃት እና በዝግጁነት ማግኘት። ያ ካለ እኔ ደስተኛ ሰው ነኝ። ትልቁ ነገር እሱ ነው። ስለሌሎቹ ሁለት ቡድኖች [ፒኤስጂና ባየርን] ስታወሩ ስንት ተጫዋቾቻቸው ነበሩ ዝግጁ የሆኑት? ሁሉም በምርጥ ብቃታቸው ላይ ነበሩ። ዋናው ነገር ይሄ ነው” ብሏል። አርቴታ ሀቨርትዝ በኤምሬትስ ስታዲየም አትሌቲኮን ለሚገጥሙበት ጨዋታ እንደሚመለስ ተስፋ ያደርጋል።
ለአርሰናል አንድ የምስራች ጋብሪኤል ማጋላየስ የሀገር ውስጥ እገዳ አለመጣሉ ነው። የፕሪሚየር ሊጉ ‘ቁልፍ የጨዋታ ክስተቶች’ (KMI) ፓናል ተከላካዩ ከኤርሊንግ ሃላንድ ጋር በነበረው ግጭት ከሜዳ መውጣት ነበረበት ብሎ ወስኗል። አርሰናል በማንቸስተር ሲቲ 2-1 በተሸነፈበት ጨዋታ ጋብሪኤል ቢጫ ካርድ ብቻ ነበር የተመለከተው። አርቴታ በፓነሉ ውሳኔ መገረሙን ገልጾ፡ “ዕድለኛ ነን ብዬ አላስብም” ብሏል።
አርቴታ ተጫዋቾቹ ፕሪሚየር ሊጉን እና ሻምፒዮንስ ሊጉን ለማሸነፍ የሚደረገውን ፈተና እንዲቀበሉ አሳስቧል። “ምን ሊመጣ እንደሚችል እናውቃለን። መግፋት አለብን። እያንዳንዱ ተጫዋች ራሱን መምራት እና የዚህን ወቅት ኃላፊነት መውሰድ አለበት፤ ምክንያቱም አሁን የሚኖራችሁ ተፅዕኖ የክለቡን ታሪክ የሚወስን ይሆናል። ይህ በጣም ትልቅ ነገር ነው” ሲል በቁርጠኝነት ተናግሯል።