በሌላ በኩል ኮርቱዋ ጆሴ ሞሪንሆ የተፈጠረውን ድርጊት ቪኒሺየስ በሊዝበን ብቸኛዋን ግብ ካስቆጠረ በኋላ ካደረገው ደስታ አገላለጽ ጋር ማያያዛቸው ቅር እንዳሰኘው ገልጿል። ፕሪስቲያኒ የዘረኝነት ስድብ ሳይሆን የግብረ ሰዶማውያን ጥላቻ (homophobic) ስድብ ነው የተጠቀምኩት የሚል መከራከሪያ ሊያቀርብ ይችላል ለሚባለው ወሬ ሲመልስም፥ “ያም ቢሆን እኩል መጥፎ ነው” ሲል አቋሙን ገልጿል።
ባለፈው ማክሰኞ በኤስታዲዮ ዳ ሉዝ በተካሄደው ጨዋታ ቪኒሺየስ ለዳኛው ፍራንሷ ሌቴክሲየር ፕሪስቲያኒ የዘረኝነት ስድብ እንደሰደበው ካሳወቀ በኋላ ጨዋታው ለ10 ደቂቃ ተቋርጦ ነበር። የቡድን አጋሩ ኪሊያን ምባፔም ተጋጣሚው ቪኒሺየስን አምስት ጊዜ “ዝንጀሮ” ብሎ እንደሰደበው ከጨዋታው በኋላ ከሷል። ዩዌፋ ምርመራ እያደረገ ባለበት ወቅት ቤንፊካ ተጫዋቹ ላይ ተጥሎበት የነበረውን የአንድ ጨዋታ ጊዜያዊ ቅጣት ይግባኝ በማለቱ ፕሪስቲያኒ ለመልሱ ጨዋታ ወደ ማድሪድ ተጉዟል።
የማድሪድ ዋና አሰልጣኝ አርቤሎአ “ከዚህ በፊት ከነበረው የተለየ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ትልቅ ዕድል አለን” ብሏል። “ዩዌፋ የፀረ-ዘረኝነት ባንዲራ ሲያነግብ ቆይቷል፤ አሁን ደግሞ ይህንኑ ከቃል ባለፈ በተግባር የምናሳይበት፣ ከጨዋታ በፊት ከሚወጡ የሚያማምሩ መፈክሮች እና ባነሮች በላይ እውን የምናደርግበት አጋጣሚ አለን” ሲል ተናግሯል።
ኮርቱዋ በበኩሉ “ይህ ለእግር ኳስ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ለማቆም ጥሩ ወቅት ነው። በመቀየሪያ ክፍል ውስጥ ቪኒሺየስ ምን እንደነገረን እናውቃለን። ይህ በእግር ኳስ ብዙ ጊዜ ተከስቷል፤ በሜዳ ላይ ብቻ ሳይሆን በተመልካች መቀመጫዎችም ጭምር። ይህን አሁን ማቆም አለብን። ዩዌፋ ምን ማድረግ እንዳለበት ይወስናል – የተጫዋቾች ፍላጎት እዚህ ላይ ቦታ የለውም – ነገር ግን እርምጃ መውሰዱ ጥሩ መልዕክት ያስተላልፋል” ብሏል።
“ከፕሪስቲያኒ ጋር በተያያዘ ሁልጊዜም የአንዱ ቃል ከሌላው ጋር ይጋጫል፤ ቤንፊካዎችም የተጫዋቻቸውን ቃል ያምናሉ። እኛ ግን 100% ከቪኒ ጋር ነን። ቪኒ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልሚያዎችን አሳልፏል፤ እንዲህ ያለ ነገር ደግሞ ተናግሮ አያውቅም። ቪኒ የሰማው ነገር 100% እርግጠኛ እንደሆነ እናውቃለን፤ እኔም አምነዋለሁ። እሱ (ፕሪስቲያኒ) አፉን ሸፍኖ ስለነበር ምን እንደተባለ በትክክል ማወቅ አንችልም፤ ስለዚህ ቤንፊካ ተጫዋቹን ይከላከላል፤ እኛም አሁን ልናደርገው የምንችለው ብዙ ነገር የለም። ዩዌፋ የሚፈልገውን መወሰን ያለበት እራሱ ነው” ሲል ቤልጄማዊው ግብ ጠባቂ አክሏል።
“በመጨረሻም ሞሪንሆ ያው ሞሪንሆ ነው፤ እንደ አሰልጣኝ ሁልጊዜም ክለብህን እና ተጫዋችህ የተናገረውን ትከላከላለህ። እኔን ትንሽ ቅር ያሰኘኝ ግን የቪኒን የደስታ አገላለጽ እንደ ምክንያት መጠቀሙ ነው። ቪኒ ምንም መጥፎ ነገር አላደረገም። የዘረኝነት ድርጊትን በደስታ አገላለጽ ማመካኘት አይቻልም” ብሏል። ፕሪስቲያኒ የግብረ ሰዶማውያን ጥላቻ ስድብ ሲጠቀም የሚያሳይ ምስል አለ ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስም፡ “ከጨዋታው በኋላ ኦሬሊየን (ትቹአሜኒ) ያንን ብሎ ነበር። ለእኔ ያም ቢሆን እኩል መጥፎ ነው። እነዚያም የጥላቻ ስድቦች ናቸው፤ እኩልም ክብደት አላቸው። በጨዋታው ወቅት በቤንፊካ ደጋፊዎች ዘንድም የዘረኝነት ምልክቶችን አይቻለሁ፤ ይህም በጣም አሳዛኝ ነው። አንድን ተጫዋች ልትወደው ወይም ልትጠላው ትችላለህ፤ ነገር ግን እንዲህ ያሉ ምልክቶች መደረጋቸው አሳፋሪ ነው” ብሏል።
“ቤንፊካ የዝንጀሮ ምልክት ያሳዩትን ደጋፊዎች ይከታተል እንደሆነ አላውቅም። ብዙ ነገሮች በአግባቡ አልተያዙም። ዘረኝነትም ሆነ የግብረ ሰዶማውያን ጥላቻ፤ እነዚህን ነገሮች በፍጹም ልንቀበላቸው አንችልም። እዚያ ጋር አፉን ባይሸፍን ኖሮ ምን ሊል እንደሚችል መገመት እንችላለን” ሲል ተናግሯል።
ቤንፊካ ወደ ማድሪድ ከመጓዙ በፊት የክለቡ ፕሬዝዳንት ሩይ ኮስታ ተጫዋቻቸው ፕሪስቲያኒ ንፁህ መሆኑን በድጋሚ ገልጸዋል። “ምን ተባለ ምን አልተባለ የሚለውን ለማወቅ ሜዳ ውስጥ አልነበርኩም፤ ነገር ግን እንደምትገምቱት በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ብዙ ነገር ሊባል ይችላል። እኛ ግን በተጫዋቻችን ቃል እናምናለን፤ ምክንያቱም ከዚያ በላይ በቤታችን ያሉትን ተጫዋቾች እናውቃቸዋለን” ብለዋል የቀድሞው የፖርቱጋል አማካይ። “ስለዚህ ፕሪስቲያኒ እንደ ዘረኛ ሰው እየተሰቀለ ነው፤ እሱ ግን ከዘረኝነት የራቀ መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፤ ለዚህም ነው በእሱ ላይ እንዲህ ያለ እምነት ያለን። ቤንፊካ ሁሉንም የሚያቅፍ፣ የዘረኝነት ተቃዋሚ ክለብ ነው፤ በቡድኑ ውስጥም ዘረኛ ተጫዋቾችን በፍጹም አይፈቅድም። ይህንን ነጥብ ግልጽ ላደርገው እፈልጋለሁ” ሲሉ አክለዋል።