League Table

አሌክሳንደር ኢሳክ በሚያዝያ ወር ወደ ጨዋታ እንደሚመለስ አርኔ ስሎት ገለጹ

የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ አርኔ ስሎት አጥቂው አሌክሳንደር ኢሳክ ከጉዳቱ አገግሞ በሚያዝያ ወር ለቡድኑ ዝግጁ እንደሚሆን ይጠብቃሉ። ስዊድናዊው አጥቂ በታህሳስ ወር ከቶተንሃም ጋር በተደረገው ጨዋታ የግራ እግሩ ላይ በደረሰበት ስብራት እና የቁርጭምጭሚት ጉዳት ምክንያት ቀዶ ጥገና ተደርጎለት የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ቀለል ያሉ ልምምዶችን ጀምሯል።

ኢሳክ እንደ ማገገሚያው አካል በዚህ ሳምንት ሩጫ የጀመረ ሲሆን፣ ሂደቱ በዚሁ ከቀጠለ በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ከቡድኑ ጋር ልምምድ እንደሚጀምር ተገልጿል። ዋና አሰልጣኙ ስለ ሁኔታው ሲናገሩ “በመጋቢት መጨረሻ ወይም በሚያዝያ መጀመሪያ አካባቢ ከቡድኑ ጋር እንደሚቀላቀል ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል። አክለውም “ከቡድኑ ጋር ተቀላቀለ ማለት ግን ወዲያውኑ ለጨዋታ ዝግጁ ነው ማለት አይደለም፤ ለወራት ያህል ከሜዳ ርቆ እንደመቆየቱ ለጨዋታ ብቁ ለመሆን ጊዜ ይወስድበታል። ከኒውካስል ያስፈረምነውን አይነት ብቃቱን ለማሳየት ጊዜ እንደሚፈልግ ካለፈው ጉዳቱ አይተናል” ሲሉ አስረድተዋል።

ኢሳክ በክረምት በ125 ሚሊዮን ፓውንድ ከኒውካስል ሊቨርፑልን ከተቀላቀለ በኋላ በ16 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ሶስት ጎሎችን አስቆጥሯል። ስዊድናዊው ተጫዋች ያለ ቅድመ-ውድድር ዝግጅት ቡድኑን የተቀላቀለ ሲሆን፣ በጥቅምት ወር በደረሰበት የብሽሽት ጉዳት ምክንያት አራት ጨዋታዎች አምልጠውት እንደነበር ይታወሳል።

ቡድናቸው እሁድ እለት ከኖቲንግሃም ፎረስት ጋር የሚጫወተው ስሎት፣ “አሌክስ በዚህ ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ በሩጫ ጫማዎቹ ሜዳ ላይ መታየት ጀምሯል፤ ይህ ሂደትም የራሱ የሆነ ጊዜ ይፈልጋል” ብለዋል። “ቀጣዩ ደረጃ ኳስ ይዞ መስራት ነው፣ ይህም ማንኛውም ተጫዋች የሚወደው ነገር ነው። ከዚያም ከቡድኑ ጋር ይቀላቀላል። የማገገሚያ ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ መሄዱ ግን ደስ የሚል ሲሆን፣ ይህም ለእሱ እና ለህክምና ክፍላችን የሚሰጥ አድናቆት ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።