በታሪክ ትልልቅ ከሚባሉ ዝውውሮች መካከል አሌክሳንደር ኢሳክ በ125 ሚሊዮን ፓውንድ፣ ፍሎሪያን ዊርትዝ በ116 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲሁም ሁጎ ኤኪቲኬ በ69 ሚሊዮን ፓውንድ ቡድኑን ተቀላቅለዋል። ሆኖም ስሎት ተቺዎች በክረምቱ ቡድኑ ከፍተኛ ሽያጭ ማድረጉን የዘነጉት ይመስላል ብለዋል። “በእንግሊዝ ውስጥ ተጫዋቾችን የሚሸጡ ክለቦች መኖራቸውን ማንም የለመደው አይመስልም” ሲሉ ተናግረዋል። “ብዙውን ጊዜ በእንግሊዝ አንድ ክለብ እንደ እኛ 450 ሚሊዮን ፓውንድ ሲያወጣ፣ ያ ቀደም ሲል ለነበረው ታላቅ ቡድን ተጨማሪ ጥንካሬ ነው። ነገር ግን ይህ ክለብ የተለየ ሞዴል አለው፤ ማንም ይህን ለማየትም ሆነ ለመረዳት አይፈልግም። የሌሎች ቡድኖች ደጋፊዎች እና አንዳንድ ተንታኞች በ300 ሚሊዮን ፓውንድ ተጫዋቾችን መሸጣችንን ሊነግሯችሁ ስለማይፈልጉ ይህንንም መረዳት እችላለሁ።”
ስሎት አክለውም አብዛኞቹን ዋና ዋና ፈራሚዎቻቸውን ለረጅም ጊዜ መጠቀም አለመቻላቸውን ገልጸዋል። ኢሳክ ብቁ ሳይሆን ከመጣና ለመላመድ ጊዜ ከወሰደ በኋላ፣ እግሩ ተሰብሮ ከታህሳስ ወር ጀምሮ ከሜዳ ርቋል። በ26 ሚሊዮን ፓውንድ የተፈረመው ጆቫኒ ሊዮኒም ለውድድር ዘመኑ ከመሰናበቱ በፊት አንድ ጊዜ ብቻ ነው መጫወት የቻለው። ሊቨርፑል የዲዮጎ ጆታን ሞትም መቋቋም ነበረበት።
ስሎት ሲናገሩ፦ “ሊጉን አሸንፈህ 450 ሚሊዮን ፓውንድ ካወጣህ የሚጠበቀው ነገር ከፍተኛ መሆኑ ሙሉ በሙሉ ምክንያታዊ ነው። ያ የሚጠበቀው ነገር ለተንታኞች፣ ለሚዲያ፣ ለእኔ እና ለደጋፊዎችም ከፍተኛ ነበር። በክለባችን ውስጥ ያለውን ሁኔታ እና በዚህ የውድድር ዘመን ያጋጠመንን ፈተና ስንመለከት፣ የውድድር ዘመኑ ለምን በዚህ መንገድ እንደሄደ ትንሽ የበለጠ ተጨባጭ ልንሆን እንችላለን። ነገር ግን የፈለገውን ያህል ሰበብ ባቀርብም፣ አሁን ላለንበት ደረጃ አሁንም ቢሆን በቂ አይደለም” ብለዋል።
ሊቨርፑል ሉዊዝ ዲያዝን ለባየር ሙኒክ በ65 ሚሊዮን ፓውንድ እና ዳርዊን ኑኔዝን ለአል ሂላል በ46 ሚሊዮን ፓውንድ በመሸጥ ከፍተኛ ገንዘብ መልሶ አግኝቷል። ነገር ግን ይህ ለቻምፒዮንስ ሊግ የማለፍ አስፈላጊነት ላይ ያለውን ጫና አላቀለለም። ስሎት ለቲኤንቲ ስፖርት (TNT Sport) ሲናገሩ፦ “በሊቨርፑል ውስጥ ሁል ጊዜ ጫና አለ። በእኔ ላይም ሆነ ተጫዋቾቹ ላይ። ይህ ሙሉ በሙሉ የተለመደ ነው። በኤፍኤ ካፕ እና በቻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ ደርሰናል፤ ነገር ግን በሊጉ ለቻምፒዮንስ ሊግ ማለፋችንን ማረጋገጥ አለብን።”