በዩኢሲ እቅድ መሰረት፣ ከሽልማት ገንዘቡ ውስጥ 2 ቢሊዮን ዩሮ ያህሉ በአውሮፓ ለሚገኙ ሁሉም ከፍተኛ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን ፕሮፌሽናል ክለቦች እንዲከፋፈል ታስቧል። ይህም ከታዋቂዎቹ ክለቦች ውጭ ላሉት የሚሰጠውን የገንዘብ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምረዋል። በአሁኑ ወቅት ከዩኤፋ ገቢ 74 በመቶው ለሻምፒዮንስ ሊግ ክለቦች የሚሰጥ ሲሆን፣ 17 በመቶው ለኢውሮፓ ሊግ እና 9 በመቶው ደግሞ ለኮንፈረንስ ሊግ ይውላል። አዲሱ እቅድ ይህንን ክፍፍል ወደ 50-30-20 በመቶ በማጥበብ፣ ገንዘቡ በቀጥታ ለክለቦች ከመሰጠት ይልቅ ወደየሀገራቱ ሊጎች ገቢ እንዲሆን ሀሳብ ያቀርባል።
በዚህ አሰራር የየሀገሩ አንደኛ ዲቪዚዮን ክለቦች 85 በመቶውን ድርሻ በእኩልነት የሚከፋፈሉ ሲሆን፣ ቀሪው 15 በመቶ ደግሞ በታችኛው እርከን ለሚገኙ ክለቦች ይሰጣል። በአውሮፓ ውድድሮች የሚሳተፉ ክለቦችም ከዚህ ገንዘብ ድርሻቸውን የሚያገኙ ሲሆን፣ በተጨማሪም በሜዳ ላይ ለሚያሳዩት ውጤት የሚሰጠውን 1.3 ቢሊዮን ዩሮ ገደማ የሚገመት “የአፈጻጸም ክፍያ” ማግኘታቸውን ይቀጥላሉ። ይህም በሜዳ ላይ የሚመዘገብ ስኬት ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ ለማድረግ ወሳኝ ተብሎ ታምኖበታል።
ይህ የውሳኔ ሃሳብ 35 በመቶ የሚሆነውን የሽልማት ገንዘብ የሚይዘውን እና በሀገራት የሚዲያ ገበያ ዋጋ እንዲሁም በታሪካዊ ስኬቶች ላይ ተመስርቶ የሚከፈለውን የዩኤፋ “የእሴት ምሰሶ” (value pillar) በማስቀረት፣ ወደ 2 ቢሊዮን ዩሮው የጋራ ፈንድ ውስጥ እንዲካተት ያደርጋል። ዩኤፋ ከ2027 እስከ 2031 ባለው ጊዜ ውስጥ የሚዲያ መብቶች ሽያጭ በ10 በመቶ ይጨምራል ብሎ ተስፋ ያደርጋል። ፓራማውንት ድርጅት በዩናይትድ ኪንግደም እና በጀርመን የሻምፒዮንስ ሊግን የማስተላለፍ መብት አሸንፏል።
ከ140 በላይ ትናንሽ ክለቦችን የሚወክለው ዩኢሲ፣ በየዓመቱ ወደ አውሮፓ ውድድሮች የሚያልፉ ክለቦች ከሀገር ውስጥ ተፎካካሪዎቻቸው በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠር ተጨማሪ ገቢ ማግኘታቸው የልዩነት ገደልን ያሰፋዋል የሚል ስጋት አለው። የዩኢሲ ቃል አቀባይ ለጋርዲያን እንደተናገሩት “በአውሮፓ መድረክ መጫወት ለሺዎች ክለቦች ህልም ቢሆንም፣ የገንዘብ ክምችቱ በከፍተኛው ደረጃ ላይ ብቻ መሆኑ የአውሮፓ ውድድሮች በየዓመቱ ተመሳሳይ ክለቦች ብቻ የሚሳተፉባቸው እና ውጤታቸውም ተገማች እንዲሆኑ የማድረግ አደጋ አለው።”
ዩኢሲ ይህ አዲስ የክፍፍል ሞዴል በተለይ በትናንሽ እና መካከለኛ ሊጎች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ይኖረዋል ብሎ ያምናል። ለምሳሌ በኔዘርላንድስ ኤሬዲቪዚ ሊግ፣ ለአውሮፓ ውድድር ያልለፉ ክለቦች የሚያገኙት ገቢ ከ1.1 ሚሊዮን ዩሮ ወደ 4.4 ሚሊዮን ዩሮ ከፍ ይላል። የሊጉ አሸናፊ የሚያገኘው የገንዘብ መጠን ደግሞ ከግማሽ በላይ ቀንሶ ወደ 27 ሚሊዮን ዩሮ ዝቅ ይላል። ቃል አቀባዩ ሲቀጥሉም “ለስፖርቱ ትልቅ ቦታ ለሚሰጡ ወገኖች፣ በክለቦች መካከል ያለው የልዩነት መስፋፋት እና የውጤት ተገማችነት የእግር ኳስን አስማት እንዲያጠፋው እንፈቅዳለን? ወይስ መላውን እግር ኳስ የሚያጠናክር የገቢ ክፍፍል እንከተላለን?” በማለት ጠይቀዋል።
ዩኢሲ እና አባል ክለቦቹ ሌላ አማራጭ መንገድ እንዳለ ያምናሉ። ዩኤፋ እና አጋሮቹ ከኃያላን ክለቦች የሚመጣውን ፖለቲካዊ ጫና ወደ ጎን በመተው ለውጥ ለማምጣት ደፋር ከሆኑ፣ በተለይም በሱፐር ሊግ ምስረታ ውድቀት ውስጥ ተሳታፊ ከነበሩ ክለቦች የሚመጣውን ተጽዕኖ ተቋቁመው መላውን የአውሮፓ እግር ኳስ የሚጠቅም ውይይት ማድረግ ይቻላል። ምንም እንኳን ዩኢሲ በዩኤፋ ዘንድ በይፋ እውቅና ባይኖረውም፣ ሃሳቡን ረቡዕ እለት በሶፊያ በተካሄደው የአውሮፓ ሊጎች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አቅርቧል። ይህ እቅድ ከ800 በላይ ክለቦችን በአባልነት በያዘው እና ተደማጭነት ባለው የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦች (EFC) ቡድን ውስጥ ለሚገኙ ትናንሽ ቡድኖች ሳቢ ሊሆን ይችላል።