League Table

ሪያል ማድሪድን ለማሸነፍ ‘ፍጹም የሆነ ጨዋታ’ ያስፈልገናል – ጋርዲዮላ

ፔፕ ጋርዲዮላ ማንቸስተር ሲቲ ማክሰኞ በሚደረገው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የ16ቱ ዙር የመልስ ጨዋታ በሪያል ማድሪድ ላይ የደረሰበትን የ3-0 ሽንፈት ለመቀልበስ “ፍጹም የሆነ ጨዋታ” እንደሚያስፈልገው አምኗል።

ባለፈው ሳምንት በቤርናባው በተደረገው ጨዋታ የማድሪዱ ካፒቴን ፌዴሪኮ ቫልቬርዴ በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠረው የሶስት ጎሎች (ሀት-ትሪክ) ድጋፍ የአልቫሮ አርቤሎአ ቡድን ወደ ሩብ ፍፃሜው ለማለፍ ትልቅ ግምት ተሰጥቶታል። ጋርዲዮላ በቡድኑ ፊት ለፊት የተደቀነውን ፈተና በሚገባ ተረድቷል። “በብዙ መልኩ ፍጹም የሆነ ጨዋታ መሆን አለበት፤ ለዚህም ደግመን ደጋግመን እንሞክራለን” ብሏል።

“ዋናው ነገር ተጫዋቾቹ ትክክለኛ ቦታ ላይ መገኘታቸው ነው። በመጀመሪያው ጨዋታ ከአራት ወይም ከአምስት አጥቂዎች ጋር ተጫውተን አንድም ጎል አላገባንም” ሲል ጋርዲዮላ ገልጿል። “አንዳንዴ በሁለት ‘ፎልስ ናይን’ (false 9s) ተጫውተህ አምስት ጎል ታገባለህ። ዋናው ሀሳቡ እዛው ነው – መሞከር አለብን። ብዙ የተለዩ ነገሮች አያስፈልጉንም፤ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ብዙ ዕድሎችን መፍጠር እንችላለን።”

ጋርዲዮላ የ2022-23 የውድድር ዘመን የመጨረሻ ቀን ላይ አስቶን ቪላን 3-2 በማሸነፍ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ያነሱበትን ጨዋታ እንደ ማሳያ አንስቷል። በወቅቱ ሲቲ እስከ 76ኛው ደቂቃ ድረስ 2-0 ተመሪ የነበረ ቢሆንም ኢልካይ ጉንዶጋን አስደናቂውን የመመለስ ጉዞ አቀጣጥሎታል። “በ14 ደቂቃዎች ውስጥ ሶስት ጎሎችን አስቆጠርን” ብሏል ጋርዲዮላ። “በሌሎች የመመለስ ታሪኮቻችን አስገራሚ ነገሮችን አድርገናል፤ ነገር ግን ጎል ይቆጠርብን ነበር ወይም በጎል ልዩነት ወይንም በዳኞች ውሳኔ እንወጣ ነበር። እንዲህ አይነት ነገሮችን ለማሳካት በብዙ ዘርፎች ፍጹም መሆንን ይጠይቃል።”

በሻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ዙር የሶስት ጎል ልዩነትን ቀልብሰው ማለፍ የቻሉት ሶስት ቡድኖች ብቻ ናቸው። እነሱም፦ ዴፖርቲቮ ላኮሩኛ በ2003-04 የሩብ ፍፃሜ ሚላንን 4-0 አሸንፎ በድምር ውጤት 5-4 ሲያልፍ፤ ሮማ በ2017-18 የሩብ ፍፃሜ ባርሴሎናን 3-0 አሸንፎ በድምር 4-4 በሜዳው ውጪ በተቆጠረ ጎል ሲያልፍ፤ እንዲሁም ሊቨርፑል በ2018-19 የግማሽ ፍፃሜ ባርሴሎናን 4-0 አሸንፎ በድምር ውጤት 4-3 ማለፉ ይታወሳል።

“ተልዕኮው እጅግ ከባድ ነው” ብሏል ጋርዲዮላ። “በማድሪድ ላይ ከሶስት በላይ ጎሎችን ማስቆጠር ቀላል አይደለም፤ ነገር ግን እዚህ ያለነው ለእግር ኳስ ጨዋታ ነው፣ ማንኛውም ነገር ሊፈጠር ይችላል። ከደጋፊዎቻችን ጋር በመሆን ከፍተኛ መነሳሳትን መፍጠር፣ ጥሩ መጫወትና በጥንካሬ መከላከል አለብን። የጎል ዕድሎችን በአግባቡ የምንጠቀምና በደንብ የምንከላከል ከሆነ ሁልጊዜም በጨዋታው ውስጥ የመቆየት ዕድል ይኖረናል።”

ጋርዲዮላ ሰኞ እለት ቡድኑ ልምምድ እንዳይሰራ በመወሰኑ ሲቲ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር (UEFA) ቅጣት ሊጠብቀው ይችላል። ጋርዲዮላ ተጫዋቾቹ ቅዳሜ ምሽት ከዌስትሃም ጋር 1-1 ከተለያዩ በኋላ በቂ እረፍት እንዲያገኙ በማሰብ ልምምዱን ማክሰኞ ከሰዓት ለማድረግ መርጧል። የዩኤፋ ህግ “አንድ ክለብ ከጨዋታው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሙሉ ልምምድ ካላደረገ፣ ሚዲያዎች ቢያንስ ለ15 ደቂቃ የቡድኑን ዝግጅት እንዲከታተሉ ከዩኤፋ ጋር በመስማማት ሌላ አማራጭ ማመቻቸት አለበት” ይላል። ጋርዲዮላ ለዚህ ሲመልስ “ቤታቸው ቢሆኑ እመርጣለሁ። ማክሰኞ ከቀኑ 8 ሰዓት ደርሰን፣ እግሮቻችንን ትንሽ አሳርተን እንገባለን። በዚህ የውድድር ዘመን ሁለት ወይም ሶስት ጊዜ እንዲህ አድርጌያለሁ” ብሏል።