ዩናይትድ ስቴትስ ማክሰኞ ከፖርቱጋል ጋር ከምታደርገው የወዳጅነት ጨዋታ አስቀድሞ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ፖቼቲኖ፣ በአሁኑ ወቅት “ሙሉ ትኩረታቸው” አሜሪካ በምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ላይ መሆኑን ተናግረዋል። “እዚህ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ቁርጠኛ መሆኔን ሁሉም የሚያውቀው ይመስለኛል” ያሉት አሰልጣኙ፤ ቶተንሃምም ሆነ ሪያል ማድሪድ የሥራ ጥያቄ እንዳላቀረቡላቸው አረጋግጠዋል። ሪያል ማድሪድ አልቫሮ አርቤሎአን ለማሰናበት ከወሰነ ፖቼቲኖ ቀዳሚው እጩ እንደሚሆኑ ሲነገር ቆይቷል። ፖቼቲኖ ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን ቆይታ ሊያራዝሙ እንደሚችሉም ፍንጭ ሰጥተዋል። “ወደፊት ምን እንደሚፈጠር ማን ያውቃል” ያሉት አሰልጣኙ፤ “ለአዳዲስ ነገሮች ክፍት ነን። ለወደፊቱ የገባነው ውል የለም። ግን ለምን አይሆንም? እኛም ሆንን ፌዴሬሽኑ ደስተኛ ከሆንን ሂደቱን የምናየው ይሆናል። በእግር ኳስ ውስጥ በፍጹም አይሆንም አይባልም” ብለዋል።
“ነገር ግን አሁን ስለዛ የምናወራበት ጊዜ አይደለም። ትኩረታችን በዓለም ዋንጫው ላይ ነው፤ ከዓለም ዋንጫ በኋላ እንደ ፌዴሬሽኑ ራዕይና እንደ እኛ ስሜት በተለያዩ መንገዶች የምንነጋገርበት ጊዜ ይኖረናል” ሲሉ አክለዋል። ቶተንሃም ሰባት ጨዋታዎች እየቀሩት ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ብቻ ርቆ ስለሚገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ የተጠየቁት ፖቼቲኖ፣ ክለቡን ማን ቢመራውም ስፐርስ ከወራጅ ቀጠናው እንደሚተርፍ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ቶተንሃም በአሁኑ ወቅት ሮቤርቶ ዴ ዜርቢን ወዲያውኑ ሥራ እንዲጀምሩ የረጅም ጊዜ ውል በማቅረብ ላይ መሆኑ ተዘግቧል። “አሰልጣኝ ቢኖርም ባይኖርም ከሊጉ እንደሚተርፉ እርግጠኛ ነኝ” ያሉት ፖቼቲኖ፤ “ምክንያቱም እጅግ አስደናቂ ተጫዋቾች አሏቸው፤ ደጋፊዎቻቸውም የማሸነፍ ጉልበት ለመፍጠር ሁሉንም ነገር ያደርጋሉ። በእርግጥ ከባድ እንደሚሆን ይታወቃል፤ ምክንያቱም ያለው ጉልበትና ሁኔታ አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ስለዛ ክለብ ከጠየቃችሁኝ፣ በጣም የምወደው ክለብ ነው፤ በፕሪሚየር ሊጉ እንደሚቆዩም ሙሉ እምነት አለኝ” ሲሉ ንግግራቸውን አጠቃለዋል።