ሞሀመድ ሳላህ ከዘጠኝ ዓመታት ቆይታ በኋላ በዚህ የውድድር ዘመን ማብቂያ ላይ ሊቨርፑልን እንደሚለቅ ክለቡ አስታውቋል። ሊቨርፑል ባወጣው መግለጫ ሳላህ “ለደጋፊዎቹ ካለው አክብሮትና ምስጋና የተነሳ ስለ ወደፊት ቆይታው ግልጽነት ለመፍጠር ይህ ማስታወቂያ በተቻለ ፍጥነት ለደጋፊዎች እንዲገለጽ ፍላጎቱን ገልጿል” ብሏል።
እ.ኤ.አ. በ2017 ከሮማ ክለቡን የተቀላቀለው ሳላህ፣ በ435 ጨዋታዎች 255 ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን አራት ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉን የወርቅ ጫማ አሸንፏል። በሊቨርፑል ቆይታውም ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን፣ የሻምፒዮንስ ሊግን፣ የፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫን፣ የዩኤፋ ሱፐር ካፕን፣ የኤፍኤ ካፕን እና ሁለት የሊግ ካፕ ዋንጫዎችን እንዲሁም የኮሚዩኒቲ ሺልድን ማሸነፍ ችሏል።
ክለቡ አክሎም “በዚህ የውድድር ዘመን ገና ብዙ የሚቀሩ ጨዋታዎች ስላሉ፣ ሳላህ ለሊቨርፑል ምርጥ የውድድር ፍጻሜን ለማምጣት ሙሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፤ ስለዚህም የእሱን ታሪክ እና ስኬቶች በሙሉ ክብር የምናከብርበት ጊዜ እሱ አንፊልድን ሲሰናበት በዓመቱ መጨረሻ ላይ ይሆናል” ብሏል። • ተጨማሪ መረጃዎች ይከተላሉ።