በዚህ ሳምንት በጄሚ ቫርዲ ፖድካስት ላይ ቀርበው በነበረው ቃለ ምልልስ፣ ዲን ቪኤአር ከመጀመሩ በፊት በነበረው ጊዜ የነበራቸውን ትውስታዎች አጋርተዋል። “ጨዋታውን እናስጀምርና እስቲ ፊሽካ ሳንነፋ ለምን ያህል ጊዜ መቆየት እንደምንችል እንይ እንባባል ነበር” ብለዋል። “ይህንን በፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ጥቂት ጊዜ አድርጌዋለሁ፤ ቪኤአር ከመምጣቱ በፊት ማለት ነው – ፊሽካ ሳልነፋ ከ20 እስከ 25 ደቂቃ የቆየሁባቸው ጊዜያት አሉ።” በተጨማሪም “ሌላ ነገርም አደርግ ነበር፤ ከመሃል ሜዳ ክበብ ሳልወጣ ለምን ያህል ጊዜ መቆየት እንደምችል እፈትን ነበር። ይህ ለጨዋታ ያህል የማደርገው ነበር። አንድ ጊዜ 15 ደቂቃ ያህል ቆይቻለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
‘ፕሮ ሬፍ’ (Pro Ref) በተባለው የዳኞች ማህበር ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት በንግግሩ ግራ መጋባታቸው የተሰማ ሲሆን፣ አንድ ዳኛ ማንም ሳያስተውለው ለ15 ደቂቃ ያህል በመሃል ሜዳ ክበብ ውስጥ ብቻ ሊቆይ ይችላል የሚለው ሃሳብ የማይመስል ነው ተብሏል።
ዲን ጡረታ ከወጡ በኋላ በሚሰጧቸው ቃለ ምልልሶች አነጋጋሪ ሲሆኑ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። ዲን እ.ኤ.አ በ2023 በቶተንሃም እና በቼልሲ መካከል በተደረገውና በአንቶኒ ቴይለር በሚመራው ጨዋታ ላይ በቪኤአር ዳኝነት ሲሰሩ ለተፈጠረ ስህተት ጣልቃ ባለመግባታቸው ከስራቸው መታገዳቸው ይታወሳል። ቴይለርን “ጓደኛዬ” ሲሉ የጠሩት ዲን፣ በሲሞን ጆርዳን ፖድካስት ላይ ሲናገሩ ቴይለር “ካለበት ጭንቀት በላይ ሌላ ተጨማሪ ጫና እንዳይፈጠርበት” በማለት ውሳኔውን በቪኤአር ስክሪን እንዲያይ እንዳልጠየቁት ገልጸው ነበር።
ማይክ ዲን በዳኝነት ቆይታቸው በሚያሳዩት ለየት ያሉ እንቅስቃሴዎችና ለካሜራ ባላቸው ፍቅር የሚታወቁ ሲሆን፣ ደጋፊዎችም “ማይክ ዲን፣ ሁሉም ነገር ስለ አንተ ነው” የሚል ዜማ ያዜሙላቸው ነበር። ይሁን እንጂ በ22 ዓመታት የዳኝነት ዘመናቸው 561 ጨዋታዎችን በመምራትና የሪከርድ 114 ቀይ ካርዶችን በመምዘዝ በሊጉ ከነበሩ ምርጥ ዳኞች አንዱ ተደርገው ይቆጠራሉ።