ዕድሜው 44 ዓመት የሆነው ካሪክ አብዛኛውን ጊዜ የተረጋጋ ጠባይ ቢኖረውም፣ እንደ አሰልጣኝነቱ ንዴቱን የሚገልጽበት ጊዜ መኖሩን ሲጠየቅ “አዎ፣ ለእያንዳንዱ ነገር የራሱ ጊዜና ቦታ አለው” ሲል ምላሽ ሰጥቷል። አክሎም “አንዳንድ ጊዜ ውጤት ሲጠፋ እናዝናለን፤ በኒውካስሉም በነበረው ውጤት አዝነናል፣ ስለዚህ ስሜቶች ነበሩ። ስፖርት የላቀ ብቃትን የሚጠይቅ በመሆኑ በስሜት መጫወት የግድ ነው፤ ይህም አንዳንድ ጊዜ ጠንከር ያለና ጥረት የሚጠይቅ ይሆናል። እኔ ይህን ስሜት መቆጣጠር ካልቻልኩ ተጫዋቾቹ ተገቢውን ስሜት እንዲፈጥሩ መጠበቅ አይቻልም፤ ስለዚህ ይህ የሥራችን አካል ነው” ብሏል።
በተጫዋችነት ዘመኑም ቢሆን ረጋ ያለ ጠባይ የነበረው ካሪክ፣ አሁን የሚያሳየው ንዴት የታሰበበት ነው ወይስ ቁጣውን መቆጣጠር አቅቶት የሚመጣ የሚለውን ሲያብራራ “አይደለም፣ ይህ በውስጣችሁ ካለው የማሸነፍ ፍላጎት የሚመነጭ ይመስለኛል። በተለያዩ መንገዶች ሊገለጽ ይችላል፤ አንዳንድ ተጫዋቾች ዝምተኛ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ይህ ማለት ግን ግድ አይሰጣቸውም ማለት አይደለም። በውስጣቸው የሆነ ነገር ይኖራል” ብሏል። “ለራስህ የሆነ ነገር ለማረጋገጥ የምታሳየው እልህና ፍላጎት ይኖራል። በተወሰነ ደረጃ ለመጫወት በራስ መተማመንና እምነት ሊኖርህ ይገባል። ነገር ግን ስሜት የዚሁ አካል ነው። ትወና ነው አልልም፤ በወቅቱ በሚሰማኝ ስሜት ነው የምመራው። አንዳንዴ ድምፄን ከፍ ላደርግ እችላለሁ፣ አንዳንዴ ደግሞ ረጋ እላለሁ። ይህም እንደ ቡድኑ ፍላጎትና በወቅቱ እንደሚፈለገው ይወሰናል፤ የአሰልጣኝነት ዋናው ሚስጥርም ተጫዋቾቹን በትክክለኛው የአእምሮ ዝግጅት ላይ እንዲገኙ ማድረግ ነው” ሲል ገልጿል።
በሌላ በኩል ማቲያስ ደ ሊክት ህዳር 21 ቀን ዩናይትድ ክሪስታል ፓላስን 2-1 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ በጀርባ ጉዳት ምክንያት ከሜዳ ርቆ ይገኛል። ካሪክ ተከላካዩ በዚህ የውድድር ዘመን ይመለስ አይመለስ ግልጽ እንዳልሆነ ተናግሯል። “የጀርባ ጉዳት አንዳንድ ጊዜ ደህና የሆነ ሲመስልህ በድንገት ድጋሚ ስሜት የሚፈጥርብህ ዓይነት ነው። ስለዚህ በትዕግስት እየሰራንበት እንገኛለን” ብሏል። ካሪክ ደ ሊክት ቀዶ ጥገና ያስፈልገው እንደሆነ ሲጠየቅ ግን “አሁን ላይ ወደዚያ ዝርዝር ውስጥ መግባት አልፈልግም፤ ማታን ለመርዳት የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። በአሁኑ ጊዜ ጉዳዩን እየተከታተልን ነው፤ በቅርቡ ተመልሶ ሁሉም ነገር መልካም እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።