ሲቲ ይግባኝ የሚለው በውሳኔው ላይ እንጂ እስካሁን ባልተወሰነው ቅጣት ላይ አይደለም። የዳኞች ቡድን ተሳስቷል የሚል መከራከሪያ ለማቅረብ ሲቲ አዳዲስ ማስረጃዎችንና የቃል ማብራሪያዎችን ማቅረብ የሚችል ሲሆን፣ የይግባኝ ሂደቱ ካለቀ በኋላ በ30 ቀናት ውስጥ ውሳኔ ይሰጣል። ይግባኙ ውድቅ ቢሆንስ? በፕሪሚየር ሊጉ ሕግ W.97 መሠረት “የይግባኝ ቦርድ ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል” ቢልም፣ በግልግል ዳኝነት (arbitration) በኩል ለመሄድ ግን የመጨረሻ ዕድል ይኖራል። ይህ ግን በጣም ጥብቅ መስፈርቶች ያሉትና የቀደሙት አካላት የሕግ ሂደቱን አላግባብ ተጠቅመዋል ከተባለ ብቻ የሚታይ ነው። ሲቲ ከዚህ ቀደም ከፕሪሚየር ሊጉ ጋር በነበረው የንግድ ስምምነት ውዝግብ ተመሳሳይ ሂደት አልፎ ስምምነት ላይ መድረሱ ይታወሳል።
ሲቲ ጥፋተኛነቱ ከጸና ቅጣቶቹ ቀላል ከሚባሉ የገንዘብ መቀጮዎች እስከ ከሊጉ እስከመባረር ሊደርሱ ይችላሉ። በመካከሉም የነጥብ ቅነሳና መሰል እርምጃዎች አሉ። የጥፋቱ ክብደት ሲታይ ሲቲ ይግባኙ ካልተሳካለት የሚጠብቀው ቅጣት እጅግ ከባድ እንደሚሆን ይገመታል። ከሊጉ መውረድ ብቻውን መጨረሻ ላይሆን ይችላል። ሌሎች የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ሲቲ ሕግ እየጣሰ ዋንጫዎችን ሲያሸንፍ የደረሰባቸውን የገንዘብ ኪሳራ ለማስመለስ ክስ ለመመስረት እየተዘጋጁ እንደሆነ ይታወቃል። ለምሳሌ ማንቸስተር ዩናይትድ በ2017-18 የውድድር ዘመን በሲቲ ተበልጦ ሁለተኛ መውጣቱና የ21ኛ የሊግ ዋንጫ ክብረ ወሰኑን ሊነጠቅ መቻሉ ይነሳል። ከሊጉ የወረዱ ክለቦችም በሲቲ ምክንያት ነጥብ አጥተን ወርደናል በሚል ክስ ሊመሰርቱ ይችላሉ። ባለፈው የውድድር ዘመን የሕግ ወጪው ወደ 50 ሚሊዮን ፓውንድ በመጠጋቱ ክለቦች ክስ የመመስረት ፍላጎታቸው ቀንሶ ቢቆይም፣ አሁን የተገኘው ውሳኔ ግን አዲስ የክስ ማዕበል እንደሚያስነሳ እርግጥ ነው።