ስለ ቀጣይ ዓመታት የትኬት ዋጋም ከደጋፊዎች ቦርድ ጋር ተጨማሪ ውይይቶች እንደሚደረጉ ተገልጿል። የፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮን በግንቦት 31 ቀን 2025 በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 703 ሚሊዮን ፓውንድ ክብረ ወሰን የሆነ ገቢ ያስመዘገበ ሲሆን፣ የታቀደው የትኬት ዋጋ ጭማሪ 1.2 ሚሊዮን ፓውንድ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ያለመ ነበር። ክለቡ ለጭማሪው ምክንያት ያደረገው የአንፊልድ ስታዲየም የሥራ ማስኬጃ ወጪዎች ማደግን ነበር።
የሊቨርፑል ደጋፊዎች ‘አንድም ፓውንድ በስታዲየም ውስጥ አንጨምርም’ (Not a pound in the ground) የሚል ዘመቻ በማካሄድ ተቃውሞአቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል። ባለፈው የክለቡ የሜዳ ጨዋታ ከክሪስታል ፓላስ ጋር በነበረው ፍልሚያ፣ ደጋፊዎቹ በባለቤቶቹ FSG ላይ ያላቸውን ቅሬታ ለመግለጽ ስታዲየሙን በቢጫ ካርዶች አጥለቅልቀውት ነበር። ‘ስፒሪት ኦፍ ሻንክሊ’ (SOS) የተሰኘው የደጋፊዎች ማህበር የክለቡን የሐሳብ ለውጥ በደስታ ተቀብሎታል። ማህበሩ ባወጣው መግለጫ “ደጋፊዎች ላደረጉት ተቃውሞ እና ከደጋፊዎች ቦርድ ጋር ላለፉት ቀናት ለተደረገው ውይይት ምላሽ በመስጠት፣ ክለቡ የደጋፊዎችን የክፍያ አቅም ያገናዘቡ የረጅም ጊዜ መፍትሄዎችን ለመፈለግ ቃል ገብቷል” ብሏል።
ማህበሩ አክሎም፣ ከትኬት ዋጋ ጭማሪ ይልቅ ሌሎች የገቢ ምንጮችን ለማግኘት ከክለቡ ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ገልጿል። “በሚቀጥለው የውድድር ዘመን በሚደረገው የዋጋ ጭማሪ ብዙዎች ቅር ሊሰኙ እንደሚችሉ እንረዳለን፤ ነገር ግን ከዚያ በኋላ ባለው ዓመት ምንም ዓይነት ጭማሪ አይኖርም። ድምፃቸውን ላሰሙ እና ከጎናችን ለቆሙ ደጋፊዎች ምስጋናችን ይድረሳቸው። ያለ እናንተ ድጋፍ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ አንችልም ነበር” ሲል ማህበሩ ምስጋናውን አቅርቧል።
ሊቨርፑል በተጨማሪም የወጣት ደጋፊዎች (Young-adult) የትኬት ምድብን እስከ 24 ዓመት ዕድሜ ድረስ እንዲያካትት ያሰፋ ሲሆን፣ በአንፊልድ ሮድ ስታንድም ለወጣቶች የሚሆን ልዩ ክፍል እንዲዘጋጅ ወስኗል። ክለቡ በቀጣይ ከደጋፊዎች ቦርድ ጋር በመሆን ሌሎች የገቢ ምንጮችን ለመፈለግ እና የትኬት ዋጋን ለደጋፊዎች ተመጣጣኝ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቋል። ሆኖም በ2028-29 የውድድር ዘመን አማራጭ መፍትሄዎች ካልተገኙ የዋጋ ጭማሪ ሊኖር እንደሚችል ክለቡ ጠቁሟል። ክለቡም ሆነ የደጋፊዎች ቦርድ ለሁሉም ወገኖች የሚጠቅም የረጅም ጊዜ መፍትሄ ለማግኘት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።