ቪኒሺየስ በ50ኛው ደቂቃ ብቸኛዋ ጎል ከተቆጠረች በኋላ ፕሪስቲያኒ የሆነ ነገር ሲናገረው ወደ ዳኛው ፍራንሷ ሌቴክሲየር በመሮጥ አቤቱታውን አሰምቷል። ፕሪስቲያኒ ሲናገር አፉን ሸፍኖ የነበረ ቢሆንም፣ ምባፔ ግን ተጫዋቹ “ሞኖ” ወይም ዝንጀሮ የሚለውን ቃል መጠቀሙን ለብራዚላዊው ምስክርነቱን ሰጥቷል። ዳኛው የፀረ-ዘረኝነት ፕሮቶኮል መጀመሩን የሚያሳይ ምልክት ቢያሳይም፣ በተጫዋቾች፣ በአሰልጣኞች እና በዳኞች መካከል ከተደረገ ውይይት በኋላ ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታውን ቀጥለዋል። ቪኒሺየስ በማህበራዊ ሚዲያ ገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ “ዘረኞች ከምንም በላይ ፈሪዎች ናቸው። ምን ያህል ደካማ መሆናቸውን ለማሳየት ሸሚዛቸውን አፋቸው ውስጥ መክተት አለባቸው። ነገር ግን በንድፈ ሀሳብ ደረጃ የመቅጣት ግዴታ ያለባቸው ሌሎች አካላት ጥበቃ ይደረግላቸዋል” ብሏል።
ቪኒሺየስ “ምንም ፋይዳ የሌለው እና አፈጻጸሙ ደካማ የሆነ ፕሮቶኮል” ሲል የገለጸውን አሰራር ተችቷል። አክሎም “እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ መታየት አልፈልግም፤ በተለይም ዋናው ዜና ስለ ሪያል ማድሪድ ታላቅ ድል መሆን በሚገባበት ወቅት እንዲህ መሆኑ ባይመቸኝም ድምፅ ማሰማት ግን አስፈላጊ ነው” ብሏል። ምባፔ በበኩሉ “[ፕሪስቲያኒ] ቪኒሺየስን አምስት ጊዜ ዝንጀሮ ብሎ ሲሰድበው አይቻለሁ” ሲል ተናግሯል። “እንዲህ ያሉ ነገሮች ዝም ብለው እንዲታለፉ አልፈቅድም። እሱ ወጣት ተጫዋች ነው፣ በእግር ኳስ ሜዳ ላይ እንዴት እንዲህ ያለ ነገር ይባላል? ሜዳውን ጥለን ልንወጣ ነበር፣ ይሄ የቡድኑ ውሳኔ ነበር። በኋላ ምን እንደተፈጠረ አላውቅም ግን ተመለስን። እንዲህ አይነት ሰው የስራ ባልደረባ ሊሆን አይችልም፣ ዳግመኛ በሻምፒዮንስ ሊግ መጫወት የለበትም” ሲል ቁጣውን ገልጿል።
የማድሪዱ አሰልጣኝ አርቤሎኣ በበኩሉ “የቤንፊካውን ተጫዋች ምን እንዳለ ጠይቁት፣ ሁላችንም ለዛ ጥያቄ ምላሽ ይገባናል” ብሏል። “ለዘረኝነት ምንም አይነት ትዕግስት ሊኖረን አይገባም፤ በ2026 በሜዳ ላይ እንዲህ ያለ ነገር እንዲከሰት መፍቀድ የለብንም። ቪኒሺየስን ላለማመን ምንም ምክንያት የለኝም” ሲል አክሏል። ተጫዋቹ ሜዳውን ጥሎ ለመውጣት ቢወስን ኖሮ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተጠይቆ “ምንም አይነት ውሳኔ ቢወስን ከጎኑ እንደምንቆም ነግሬው ነበር። ሁልጊዜም አብረን እንታገላለን። ዳኛው ምንም እንዳልሰማ እና በዚያ ሁኔታ ውስጥ ምንም ማድረግ እንደማይችል ተናግሯል። ቪኒሺየስ የወሰነውን ሁሉ እናደርግ ነበር። ይህንን መታገስ አንችልም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
የቤንፊካው ዋና አሰልጣኝ ሆሴ ሞሪንሆ ደግሞ ችግሩ ምን እንደሆነ ከመገንዘባቸው በፊት ጨዋታው በቆመበት ወቅት ከአርቤሎኣ ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል። “ይህ ልጅ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ጎል አስቆጥሮ ለምን ጥግ ላይ ሄዶ ሞኝነት ይፈጽማል? ብዬ ነበር። በኋላ ግን ቪኒሺየስ መጫወት እንደማይፈልግ ስረዳ ስለመቀጠላችን ተነጋገርን” ብለዋል። ሞሪንሆ አክለውም “ከአርቤሎኣ እና ከምባፔ በበለጠ ሚዛናዊ ለመሆን እሞክራለሁ። ቪኒሺየስ ውሸታም ነው ማለት አልፈልግም፣ ተጫዋቼም ቅዱስ ነው ማለት አልፈልግም” ብለዋል። ሞሪንሆ መጀመሪያ ላይ ለቪኒሺየስ “ከዚህ አለም ያልሆነ ጎል አስቆጥረሃል፣ ለምን እንዲህ ታከብራለህ? ለምን እንደ ዲ ስቴፋኖ፣ ፔሌ ወይም ዩሴቢዮ በደስታ ብቻ አታከብርም?” ማለታቸውንም ገልጸዋል።